የመስቀል ደመራ በዓል ከሀይማኖትነቱ ባሻገር የኢ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የመስቀል ደመራ በዓል ከሀይማኖትነቱ ባሻገር የኢትዮጵያውያን መገለጫና የዓለም ህዝቦችን ያስደመመ የጋራ ሀብታችን ነው ::አቶ ሞገስ ባልቻ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመስቀል ደመራ በዓልን ምክንያት በማድረግ በመስቀል አደባባይ የፅዳት ዘመቻ አካሄደ

የፅዳት ተግባሩን ያስጀመሩት የከተማ አስተዳደሩ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ የመስቀል ደመራ በዓል በሚከበርበት በመስቀል አደባባይ የሁሉም ሃይማኖት መሪዎችና ምዕመናን የተሳተፉበት የፅዳት ዘመቻ ላይ በመገኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል።

አቶ ሞገስ አክለውም እኛ ኢትዮጵያውያን አንድነታችን የጥንካሬያችን መሰረት፣ መተሳሰባችን ያቆራኘን ኢትዮጵያዊ ማሰርያችን፣መከባበራችን የአብሮ መኖራችን ሚስጥርና መለያችን ሆኖ ዘመናትን ተሻግረናል ፤ ትውልዱም ይህንን ድንቅ ጥበብና ሚስጥር ይዞ እንዲቀጥልም እንሰራለን ብለዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል ከሀይማኖትነቱ ባሻገር የኢትዮጵያውያን መገለጫና የዓለም ህዝቦችን ያስደመመ የጋራ ሀብታችን በመሆኑ ለዚህ ድንቅ በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ መምህር የማነ ዘመንፈስ ቅዱስ በበኩላቸው የመስቀል በዓልን የምናከብረው በመስቀሉ የተሰራልንን ድንቅ ተዓምር ለመግለጽ ነው ብለዋል።

ቤተክርስቲያኗ በመስቀሉ የምታስተምረው ሰላምን ነው ያሉት መምህር የማነ ይህንን ሰላም በትብብር ማፅናት የሁላችንም ኃላፊነት ነው ብለዋል።

የትብብር መገለጫ በሆነው በዛሬው እለት ከቤተክርስቲያኗ ጎን መሆናቸውን ለመግለጽ የተገኙትን ሁሉ በቤተክርስቲያኗ ስም አመስግነዋል።

የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ ዋና ፀሀፊ መጋቢ ታምራት አበጋዝ የመስቀል በዓል ከሀይማኖት መገለጫነቱ ባሻገር በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በቅርስነት የተመዘገበ በመሆኑ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኩራት መሆኑን ጠቅሰው በዓሉ በሰላም ሲከበር ኢትዮጵያውያውያንን በዓለም አደባባይ በማንገስ አንድነታችንን ያጠናክራልና በልዩ ትኩረት ልናከብረው ይገባል ምክንያቱም አንዳችን ያለአንዳችን ድምቀት የለንምና ብለዋል።

በፅዳቱ ላይ የተገኙት የተለያየ እምነት ተከታይ አባቶችም መስቀል የአብሮነትና የኢትዮጵያዊነት መገለጫ መሆኑን ጠቅሰው በዓሉን በትብብርና በአንድነት በማክበርም የነበረውን ኢትዮጵያዊ ትስስራችንን እናስቀጥላለን ብለዋል።

ዛሬ ማክበሪያ ቦታውን እንዳፀዳንም ክፋትን ከውስጣችን ልናፀዳ ይገባል ያሉት የሀይማኖት አባቶቹ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮችም የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

አቶ ሞገስ ባልቻ ባስጀመሩት በዚህ የፅዳት ንቅናቄ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች፣ የአዲስ አበባ የሀይማኖት ተቋማት ጉባዔ አመራሮችና የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም የተለያየ የህብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.