የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ወረዳ 12 የሰላም ሠራዊት ሥምሪትና እንቅስቃሴን ጎበኙ፡፡
በምልከታው ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ባስተላለፉት መልዕክት የቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 12 የሰላም ሠራዊት የአካባቢውንና የአዲስ አበባን ሰላም በማስጠበቅ ያለው ተመክሮና ዝግጁነት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው፣ ይህንን ስኬታማ እንቅስቃሴ በመጪዎቹ የመስቀል ደመራና የኢሬቻ በዓላት ወቅትም አጠናክሮ በማስቀጠል አንጸባራቂ ታሪክ እንደሚጽፍ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
“ለሰላም መከበር ለምትከፍሉት መስዋዕትነት ሀገር ታመሰግናችኋለች” ያሉት ወ/ሮ ሊዲያ፣ የሰላም ሠራዊተቱ አስተማማኝ የሰላምና የልማት ደጀን በመሆን ትጋቱን እንዲቀጥል አሳስበዋል፡፡
የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ሮ ዓለምጸሐይ ሺፈራው በበኩላቸው የክፍለ ከተማው የሰላም ሠራዊት በሰላም፣ በልማትና በመልካም አስተዳደር ተግባራት ንቁ ተሳታፊ በመሆን ላበረከተውና እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋና አቅ”ርበው፣”አሁንም እናንተን ይዘን መጪዎቹን በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር ለማክበር እንደምንበቃ ጥርጥር የለንም” ብለዋል፡፡
“የቦሌ ክፍለ ከተማ የሰላም ሠራዊት ለክፍለ ከተማችሁ ሰላም በጀግንነት የምትከፍሉትን መስዋዕትነት እናደንቃለን” ያሉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ባለሥልጣን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሚኪያስ ሙሉጌታ፣ አባላቱ በጽናት ለሰላም መረጋገጥ የጀመሩትን እንቅስቃሴ እንዲያጠናክሩ አደራ ብለዋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.