ባለፉት ሁለት ቀናት በኮሪደር ልማት ስራችን የጀመርናቸውን የታክሲ እና ባስ ተርሚናሎች፣ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንጎች እንዲሁም የፒያሳ መልሶ ማልማት ስራዎች ያሉበትን ሁኔታ ተዘዋውረን ገምግመናል::
በመጀመሪያው ዙር የኮሪደር ልማት ስራችን ሰርተን ለህዝብ ክፍት ካደረግናቸው ስራዎች በተጨማሪ በከተማችን ያለውን የትራፊክ ስርዓት እንዲያሳልጡ ከጀመርናቸው 48 የመኪና ማቆሚያ እና የታክሲ/ባስ መጫኛና ማውረጃዎች ውስጥ 11 የሚሆኑት ከ 2 እስከ 3 ወለል ከመሬት በታች እና ከመሬት በላይ እየተገነቡ መሆኑን መግለፃችን ይታወሳል::
በመሆኑም በአራት ኪሎ፣ ፒያሳ ጊዮርጊስ አካባቢ፣ ቸርችል መንገድ ቴዎድሮስ አደባባይ፣ ባሻ ወልዴ አካባቢ፣ ደጎል አደባባይ አካባቢ፣ ቦሌ ድልድይ አካባቢ፣ ቦሌ መንገድ ደንበል አካባቢ፣ ሳር ቤት፣ ቀበና አካባቢ፣ መገናኛ እና ሲኤምሲ አካባቢ ከመሬት በታች ከ 2 እስከ 3 ወለል ከመሬት በታች እና ከመሬት በላይ የሆኑ የታክሲና የባስ ተርሚናሎች የግንባታ ሁኔታ በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኝ ሲሆን በታቀደው ጊዜ ውስጥ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት የሚደረግ ይሆናል::
በተጨማሪም በኮሪደር ልማት ስራችን የዋና መንገድ አካባቢ ብቻ ሳይሆን የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን ጨምሮ ከተማችንን ለመኖር ምቹ እና አለምአቀፍ ደረጃዋን የጠበቀች ለማድረግ የጀመርናቸው ልዩ ልዩ መሰረተ ልማቶችንም የሚያካትት ሲሆን እነዚህ ስራዎች ለከተማችን ነዋሪዎችም ሰፊ የስራ እድል እየፈጠሩ ናቸው::
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.