የኢሬቻ በዓል የህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር እና...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የኢሬቻ በዓል የህዝቦችን ትስስር ለማጠናከር እና የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው

የ2017 የኢሬቻ በዓል አከባበርን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መግለጫ ሰጥቷል።

ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ጋር ስትነጻጸር ብዙ የአደባባይ በዓላት ያላት ሲሆን ይህም ከህብረ ብሔራዊ ብዝሃ ባህል ጸጋዎቿ የመነጨ ነው።

ስለዚህ እነዚህ በዓላት እሴቶቻቸውን ጠብቀው እንዲከበሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል መግለጫውን የሰጡት የባህል ፣ ኪነጥበብ እና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊዋ ሂሩት ካሳው(ዶ/ር) ።

ከእነዚህ በዓላት አንዱ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ በድምቀት የሚከበረው የኢሬቻ በዓል ነው ያሉት ሀላፊዋ የኢሬቻ በዓል በመስከረም ወር ከክረምት ወደ በጋ ፣ ከጭለማ ወደ ብርሃን መሸጋገርን በማሰብ ለፈጣሪ ምስጋናን ለማቅረብ የሚከበር የአደባባይ በዓል ነው ብለዋል።

ኢሬቻ ሲከበር ህዝቡ በተለያየ አልባሳት እና ጌጣጌጥ አሸብርቆ የሚከበር በዓል በመሆኑ ለጥበብ ውጤቶች ፈጠራና ሽያጭ አስተዋጽኦው የጎላ ነውም ሲሉ ገልጸዋል።

በዓሉ በአዲስ አበባ ከተማ ብዙ ህዝብ በተገኘበት የሚከበር በመሆኑ የህዝቦች ግንኙነትን በማጠናከር እና እሴት እና ባህላቸውን እንዲለዋወጡ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለውም ነው ያሉት።

አዲስ አበባ ከተማ የቱሪስት ከተማ እየሆነች መምጣቷ የተገለጸ ሲሆን ከተማዋን የቱሪስት መሸጋገሪያ ብቻ ሳይሆን መዳረሻ ለማድረግ የሚያስችሉ መስዕቦች የለሙባት ከመሆኗም ባሻገር የአደባባይ በዓላት የቱሪስት መስዕብነቷን ያሳድጋሉ ተብሏል።

ኢሬቻን መሰል የአደባባይ በዓላት ደግሞ የሀገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያደርግም ነው ሀላፊዋ የገለጹት።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ሚኤሳ ኤሌማ(ዶ/ር) በበኩላቸው ኢሬቻ ሰው ከሰው እንዲሁም ከተፈጥሮ ጋር ሰላምን የሚያሰፍንበት እና ስለ ሰላም የሚሰበክበት የሰላም በዓል ነው ብለዋል።

በተለይም የዘንድሮው የኢሬቻ በዓል አዲስ አበባ ከተማ በኮሪደር ልማት እና መልሶ ማልማት ስራዎች አምራና ደምቃ ባለችበት የሚከበር በመሆኑ ልዩ ያደርገዋል ያሉት ሀላፊው በከተማዋ አምስቱም መግቢያ በሮች እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።

በዓሉን ለማክበር በከተማዋ የተለያዩ ዝግጅቶች ተደርገዋል ያሉት ሀላፊው የኢሬቻ ኤግዚብሽን እየተካሄደ ነው ብለዋል፡፡

በቀጣይም የኢሬቻ ፎረም የሚካሄድ መሆኑን ገልጸው በዓሉ እሴቱን ጠብቆ በድምቀት እንዲከበር አስፈላጊው ዝግጅት መደረጉን አመልተዋል፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.