እሬቻ የጋራ ሃብታችን፣ የሁላችንም ኩራት፣ የአብ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

እሬቻ የጋራ ሃብታችን፣ የሁላችንም ኩራት፣ የአብሮነታችን መድመቂያና ዘመናትን በህብር የተሻገረው የአብሮ መኖራችን ሚስጥር ነው"አቶ ከፍያለው ተፈራ የኦሮሚያ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኢሬቻ በዓል የሚከበርበት አካባቢ የፅዳት መርሀ ግብር አካሄደ።

የፅዳት መርሐ ግብሩ በኦሮሞ ባህል መሰረት በአባገዳዎችና በሀደሲንቄዎች በምረቃ ስነ ሰርዓት ተጀምሯል።

ፅዳቱን ያስጀመሩት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ ስራ አስኪያጅ ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ኢሬቻ ሰላም በመሆኑ በዓሉን ስናከብር ለሰላምና ለአብሮነት ያለንን ቁርጠኝነት በማሳየታችን ነው ብለዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የብሔር ብሔረሰቦችን ባህልና እሴት አክብራ የምትንቀሳቀስ መሆኗን ያስታወሱት ኢንጂነሩ የዛሬው ፅዳት ቦታውን ከማፅዳት ባለፈ የጋራ አብሮነታችንን የምናሳይበት ነውም ብለዋል።

በፅዳት መርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ በበኩላቸው የኢሬቻ በዓል የሰላም የአብሮነት፤ የተለያየ የሚገናኝበት፤ ከሁሉ በላይ ፈጣሪ የሚመሰገንበት በመሆኑ ሁላችንም ተቀራርበን አብሮነታችንን ከፍ እያደረግን አንድነታችንን እያፀናን ልናከብር ይገባል ብለዋል ፡፡

አቶ ከፍያለው አክለውም በዓሎቻችን የጋራ ሃብቶቻችን፣ የሁላችንም ኩራት፣ የአብሮነታችን መድመቂያና ዘመናትን በህብር የተሻገረው የአብሮ መኖራችን ሚስጥር ናቸውም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ እሴቶች ያላት ሀገር ስለሆነች ይህንን እሴት በአግባቡ ከተጠቀምን ለአንድነታችን ለእድገታችን ትልቅ አቅም ነው ያሉት አቶ ከፍያለው

እሬቻ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ፍትህ የሚሰጥ በመሆኑ እንዲህ ዓይነት እሴቶቻችንን በአግባቡ ከተጠቀምን ለአብሮነታችን ትልቅ አቅም ነው ብለዋል።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙባረክ ከማል በበኩላቸው እሬቻ የገዳ ስርዓት ካጎናፀፈን እሴቶች አንዱና ዋናው ነው። እሬቻ ሲከበር ጎላ ብሎ ከሚከወኑ ጉዳዮች አንዱና ዋናው ምስጋና ነው። ስለዚህ ይህ የምስጋና በዓል በክፍለ ከተማችን በመከበሩ ለእኛ ለቂርቆስ ነዋሪዎች ትልቅ አጋጣሚ ነው ብለዋል

እሬቻ በከተማችን መከበር ከጀመረ ጊዜ አንስቶ ህዝባችን በኢኮኖሚው ዘንድ ትልቅ ጥቅም እያገኙ ነውና ይህ በዓል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የበኩላችንን ድርሻ ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

በፅዳት መርሐ ግብሩ ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ፣ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ ፣የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሙባረክ ከማልን ጨምሮ የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም አባገዳዎችና ሀደሲንቄዎች፣ የተለያዩ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ታዋቂ ሰዎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.