በኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል አከባበር ወቅት የትራፊክ መጨናነቅ እንዳይፈጠር የተወሰኑ መንገዶች ለተሽከርካሪ ዝግ ስለሚሆኑ አሽከርካሪዎች አማራጭ መንገዶችን እንዲጠቀሙ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
በርካታ ህዝብ የሚታደምበት እና አባገዳዎች፣ ሀደ ስንቄዎች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የሚገኙበት የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ/ም በአዲስ አበባ ይከበራል፡፡
በዓሉ በሠላም እንዲከበር የፀጥታ አካላት ትኩረት ሰጥተው ወደ ተግባር በመግባት እየሰሩ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅሶ በተለይ በዓሉ ወደሚከበርበት ስፍራ የሚመጡ ታዳሚዎች ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ መኖሩን ተገንዝበው አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ተጠይቋል፡፡
ከዚህ ቀደም የተከበሩ ኃይማኖታዊና ብሔራዊ በዓላት በሠላም እንዲከበሩ ህብረተሰቡ ከፀጥታ ኃይሉ ጋር በመተባበር ወሳኝ ስራ ማከናወኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውሶ የዘንድሮው የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል በሠላም እንዲከበር የበዓሉ ታዳሚዎች እና የከተማው ነዋሪ የተለመደውን ትብብር እንዲያደርጉ በፀጥታ አካላት ስም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
በመሆኑም የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓል ተከብሮ እስከሚጠናቀቅ
ከቅዱስ ኡራኤል አደባባይ ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ቅዱስ ኡራኤል አደባባይ ላይ
ከቦሌ አቅጣጫ ወደ መስቀል አደባባይ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ኦሎምፒያ አደባባይ ላይና ታች እንዲሁም ግራና ቀኝ
ከመስቀል ፍላወር ወደ ኦሎምፒያ የሚወስደው መንገድ ጋዜቦ አደባባይ ላይ
ከአጎና ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ ለከባድ ተሽከርካሪ አጎና ሲኒማ አጠገብ እንዲሁም ለቀላል ተሽከርካሪ ጥላሁን አደባባይ (አራተኛ ክፍለ ጦር ላይ)
ከለገሀር መብራት ወደ መስቀል አደባባይ ለገሀር መብራት ላይ
ከቴሌ ማቋረጫ ወደ ስታድዮም ለሚጓዙ ቴሌ ማቋረጫ
ከራስ ሆቴል ወደ ስታድዮም ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ራስ ሆቴል ላይ
ከሃራምቤ መብራት ወይም ከአምባሳደር ሲኒማ ወደ መስቀል አደባባይ ሃራምቤ መብራት ላይ
ከብሔራዊ ቤተ መንግስት ወደ መስቀል አደባባይ የሚወስደው መንገድ ብሔራዊ ቤተ መንግስት አጠገብ
ከካዛንቺስ ሼል ወደ ባምቢስ የሚወስደው መንገድ ካዛንቺስ ሼል አጠገብ እንዲሁም
ከጁፒተር ሆቴል ወደ ECA የሚወስደው መንገድ ባምቢስ ሳልኮት ህንፃ አጠገብ
ከመስከረም 24 ቀን 2017 ዓ/ም ከቀኑ 6፡00 ሰዓት ጀምሮ ፕሮግራሙ እስከሚጠናቀቅ ድረስ መንገዶቹ ለተሽከርካሪ ለጊዜዉ ዝግ እንደሚሆኑ አስታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ የሸገር ከተማ አካባቢዎች በርካታ ህዝብ በዓሉን ለማክበር ከዋዜማው ጀምሮ ወደ ከተማችን የሚገባ በመሆኑ መላው ህብረተሰብ ተገቢውን አክብሮት በመስጠት የእንግዳ ተቀባይነት እሴታችንን አጉልቶ ሊያሳይ እንደሚገባ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውሶ በዓሉ በሚከበርበት ዙሪያ እና በአካባቢው በግራና በቀኝ ለረጅምም ሆነ ለአጭር ጊዜ ተሽከርካሪ አቁሞ መሄድ ፍፁም የተከለከለ መሆኑን ገልጿል፡፡
በመጨረሻም ህብረተሰቡ ለፀጥታ ስጋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙት በ011-1-11-01-11 እንዲሁም በ991 ነፃ የስልክ መስመር ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.