የ2017 ዓ.ም የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ ደማቅና ሰላ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የ2017 ዓ.ም የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ ደማቅና ሰላማዊ ሆኖ እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን ጥምር የፀጥታ ኃይሉ አስታወቀ

ባሳለፍነው ሳምንት የተከበረው የ2017 ዓ.ም የመስቀል ደመራ በዓል አከባበር የፀጥታ ኃይሉ በሰራው የተጠናከረ ቅንጅታዊ ስራ እና በህብረተሰቡ ተሳትፎ በሰላም መጠናቀቁን ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ጠቅሷል።

ቅዳሜ መስከረም 25 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚከበረው የ2017 ዓ.ም የኢሬቻ ሆራ ፊንፊኔ በዓላዊ ትውፊቱን ጠብቆ በድምቀትና በሰላም እንዲጠናቀቅ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቆ ወደ ስራ መግባቱን አስታውቋል።

የፀጥታ አካላቱ ለሚያከናውኗቸው ተግባራት በተዘጋጀው የማስፈፀሚያ ዕቅድ ላይ በአዲስ አበባ ፖሊስ መሰብሰቢያ አዳራሽ ውይይት ሲካሔድ፥ የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ መድረኩን መርተውታል።

በውይይቱ ላይ እንደተገለፀው በዓሉ ባህላዊ ስርዓቱን ጠብቆ በሰላም እንዲከበር ለማስቻል በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ በርካታ የፀጥታ ኃይል ተሰማርቶ ወደ ስራ መግባቱ የተገለፀ ሲሆን፤ የበዓሉን ገፅታ የሚያጠለሹ ግጭት ቀስቃሽ ጽሁፎችና መልዕክቶችን እንዲሁም ከበዓሉ ጋር ግንኙነት የሌላቸውን ቁሳቁስ ይዞ ወደ በዓሉ ስፍራ መምጣት ፈፅሞ የተከለከለ መሆኑም በመድረኩ ላይ ተነግሯል።

ክብረ በዓሉን ለእኩይ ዓላማ ለመጠቀም የሚደረጉ ማንኛውም ዓይነት ሕገ-ወጥ ተግባራት በፍፁም ተቀባይነት እንደሌላቸውና ይህን ለማድረግ በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገልጿል።

በዓሉ በሰላም እንዲከበር በርካታ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች መከናወናቸውን የጠቀሰው ጥምር የፀጥታ ኃይሉ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የአሰሳ እና ፍተሻ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን አመልክቶ፤ ህብረተሰቡ የፀጥታ አካላቱ ለሚያከናውኑት የፍተሻ ስራ ተባባሪ እንዲሆን ጠይቋል።

በመስቀል ደመራ በዓል ላይ የተሰራውን የቅንጅት ስራ በማጠናከር የኢሬቻ በዓልም በሰላም እንዲጠናቀቅ ለማስቻል የፀጥታ ኃይሉን በማገዝ ሃላፊነታቸውን የሚወጡ መላው የከተማዋ የሰላም ሰራዊት አባላት እና ባለድርሻ አካላት በተግባሩ ላይ እንደሚሳተፉ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ ጠቁሟል።

በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ የተለያዩ የሸገር ከተማ አካባቢዎች በርካታ ህዝብ በዓሉን ለማክበር ወደ ከተማችን እንደሚገባ ታሳቢ በማድረግ መላው ህብረተሰብ ከፀጥታ ኃይሉ ጎን በመቆም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥምር የፀጥታ ኃይሉ መልዕክት አስተላልፏል።

ህብረተሰቡ ለሰላም እንቅፋት የሆኑ አጠራጣሪ ነገሮች ሲያጋጥሙ በ011-1-26-43-59፣ 011-5-52-63-02/03፣ 011-5-52-40-77፣ 011-5-54-36-78 እና 011-5-54-36-81 እንዲሁም በ987፣ 991 እና 816 ነፃ የስልክ መስመሮች ጥቆማ በመስጠትና አስፈላጊውን ትብብር በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።

 

 

 

 

 

 


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.