የኢሬቻ በዓልን ለመታደም የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት አድርገናል- የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ አባ ገዳዎች፣ሃደ ሲንቄዎች፣ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎችና የስራ ኃላፊዎች የተገኙበት የኢሬቻ ፌስቲቫል ተካሄዷል፡፡
በመርሐግብሩ ላይ የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ አይዳ አወል፣ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ምክትል ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ቆንጂት ደበላ ፣የአዲስ አበባ ከተማ የውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ዘሪሁን አባተ እና ሌሎች የስራ ሀላፊዎች ተገኝተዋል።
የኦሮሞ ህዝብ የጥንታዊ ስልጣኔ መገለጫዎችን በማስተዋወቅ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደረገ ማህበረሰብ ነው ያሉት የአዲስ ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ አይዳ የኢሬቻ በዓልም በኦሮሞ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ህብርና ብዝሀነትን በሚያሳይ መልኩ በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ እንደሚከበር ተናግረዋል።
ኢሬቻ ከሚያንፀባርቀው ባህላዊ ቀለም በተጨማሪ ሰላም፣ፍቅር፣ አንድነትና ፍትህን የሚሰብክ በዓልም ነው ብለዋል።
የከተማዋ ነዋሪ በኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል እንግዶችን በፍፁም ጨዋነት እንዲቀበልም ስራ አስፈፃሚዋ ጥሪ አቅርበዋል።
በፌስቲቫሉ የተገኙ የክፍለ ከተማው ነዋሪዎችም የኢሬቻ በዓልን ለመታደም ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች የሚመጡ እንግዶችን ለማስተናገድ ዝግጅት ስለማድረጋቸው አንስተዋል።
በፌስቲቫሉ ላይ የኦሮሞ ባህላዊ ምግቦች፣ባህላዊ አልባሳትና ባህላዊ ጭፈራዎች በተሳታፊዎች ቀርበዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.