ዛሬ የ2017 የኢሬቻ ፎረም አካሂደናል።

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ዛሬ የ2017 የኢሬቻ ፎረም አካሂደናል።

6ኛው ዙር የኢሬቻ ፎረም አባ ገዳዎችና ሀደ ሲንቄዎች፣ አምባሳደሮች፣ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት፣ የፌደራል ክልልና ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ ፎሌዎች፣ ዲያስፖራዎች እንዲሁም የከተማችን ነዋሪዎች በተገኙበት በዓድዋ ድል መታሰቢያ በድምቀት አካሂደናል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ የብዝሃ ማንነቶች ባለ ፀጋ እንደመሆኗ መጠን ህዝባዊ እና ሀይማኖታዊ በዓላት አንድነትን፣ ፍቅርንና የህዝቦች ትብብርን በማፅናት ረገድ አይነተኛ ሚና የሚጫወት ሲሆን የኢሬቻ በዓል የሰላም፣ የእርቅ፣ የአንድነት፣ የአብሮነት እንዲሁም የወንድማማችነትና እህትማማችነት በዓል ሆኖ በመከበር ላይ ይገኛል።

ኢሬቻ የገዳ ስርዓት አንዱ ምሰሶ ሲሆን የምስጋና፣ የሰላም እና የወንድማማችነት ተምሳሌት ሆኖ የኦሮሞ ህዝብ ከጥንት ጀምሮ ከፈጣሪ፣ ከተፈጥሮ እና ከሰው ሁሉ ጋር ያለውን ግንኙነት የሚያድስበት ነው። በኢሬቻ የተራራቀ ይቀራረባል፤ የተቀያየመም ይታረቃል።
የሆራ ፊንፊኔ ኢሬቻ  ለረጅም ዓመታት ተቋርጦ የቆየ ቢሆንም   ለውጥን ተከትሎ ወደ ቀድሞ የማክበሪያ ስፍራው ተመልሶ በሁሉም ህዝቦች ወንድማማችነት ደምቆ መከበር ከጀመረ እነሆ ዘንድሮ 6ኛ ዓመቱን ይዟል።

ኢሬቻ አሁን ከባህላዊ ክንውንነቱ አልፎ የከተማችንና የሀገራችን የቱሪዝም መስህብ እና ሰፊ የገቢ ምንጭ ወደመሆን ተሸጋግሯል።
በዚሁ አጋጣሚ ለመላው ህዝባችን እንኳን ለ2017 የኢሬቻ በዓል አደረሳችሁ እያልኩ የሁሉም ቤት የሆነችው አዲስ አበባችን ለክብረበዓሉ ወደ ከተማችን የሚመጡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገራት እንግዶቿን መቀበል ላይ የምትገኝ ሲሆን ውድ የከተማችን ነዋሪዎች እንግዶችን ለመቀበል እያደረጋችሁት ላለው መስተንግዶ በራሴ እና በከተማ አስተዳደሩ ስም ከልብ አመሰግናለሁ።

ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ

በድጋሚ እንኳን አደረሰን!
ከንቲባ አዳነች አቤቤ


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.