ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማትን በተመለከተ ከመንግስት እና ከግል ሚድያ ጋዜጠኞች ለተነሱልኝ ጥያቄዎች ማብራሪያ ሰጥቻለሁ።
በክቡር ጠቅላይ ሚንስትራችን በተሰጠን የስራ መመሪያ መሰረት የተጠኑት የሁለተኛ ዙር ኮሪደሮች ስምንት ሲሆኑ፣ ለህዝብ ያለእረፍት እየሰራን ከህዝብ የምንደብቀው ምንም ስለሌለ በዝርዝር ማብራሪያ ሰጥቻለሁ። ማብራሪ መስጠቱ ለወደፊትም ይቀጥላል።
የኮሪደር ልማት ዋና አላማዉ ከተማችንን ለመኖር ምቹማድረግ፣ ማደስ፤ ገፆታዋን ማሻሻል እና ከልማቱ ማንም ወደ ኋላ ሳይቀር ሁሉም ተጠቃሚ እንዲሆን ማስቻል ነዉ።
ሁለተኛው ዙር የኮሪደር ልማት ስራችን በአጠቃላይ 2817 ሄክታር መሬት በሚሸፍን እና 132 ኪ.ሜ ርዝመት ባለው ቦታ ላይ የሚገነባ ሲሆን፣ በግንባታ ስራው ከተካተቱ የመሰረተ ልማት ስራዎች ውስጥ የመንገድ ግንባታ፣ የአረንጓዴ ቦታዎች ግንባታ፣ የብስክሌት መንገድ፣ የእግረኛ መንገድ፣ የህፃናት መጫወቻዎች፣ የታክሲና አውቶቢስ መጫኛና ማውረጃ ተርሚናሎች፣ የመኪና ማቆሚያ ፓርኪንጎች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ የህዝብ መጸዳጃ ቦታዎች፣ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመሮች ፣ ደረጃውን የጠበቀ የከተማ መብራት፣ የቴሌኮም መሰረተ ልማት እንዲሁም የደህንነት መጠበቂያ ቴክኖሎጂዎች ዝርጋታ ስራ ተጠቃሾቹ ናቸው።
ስራዉ በዋናነት በከተማው አቅም እና በጀት የሚከናወን ሲሆን ኢትዮ ቴሌኮም፣ አርተፊሻል ኢንተለጀንስ፤ የመብራት አገልግሎት እና የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በዚህ ውስጥ መሰረተ ልማታቸውን በመዘርጋትና ከተማዋን ስማርት ሲቲ በማድረግ በኩል ትልቅ እገዛ የሚያደርጉ ይሆናል።
ሁለተኛውን ዙር የኮሪደር ልማት ስራችንን በፍጥነት ለማጠናቀቅ በቂ ቅድመዝግጅት ያደረግን ሲሆን፣ በመልሶ ማልማት ሲኖሩ ከነበሩበት ለመኖር ምቹ ያልሆነ ጎስቃላ አካባቢዎች ለተነሱ ነዋሪዎች የመኖሪያ ቤቶችን፣ በቂ የመስሪያ ሼዶችን፣ ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ እንዲሁም ከ 500 በላይ የሚሆኑ የንግድ ሱቆችን ለነዋሪዎቻችን ዝግጁ አድርገናል። በተመሳሳይ ምትክ መሬት እና ካሳ አዘጋጅተናል።
በሁለተኛ ዙር የተለዩት ኮሪደሮች:-
1. ካሳንቺስ- እስጢፋኖስ-መስቀል አደባባይ- ሜክሲኮ- ቸርችል-አራት ኪሎ ኮሪደር እና መልሶ ማልማት ስራ (የኮሪደሩ ርዝመት 40.4 ኪ/ሜ)
2. ጫካ ፕሮጀክት (ሳውዝ ጌት)- መገናኛ- ሃያ ሁለት- መስቀል አደባባይ ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 7.1 ኪ.ሜ)
3. ሲኤምሲ- ሰሚት- ጎሮ- ቦሌ ቪአይፒ ተርሚናል ኮሪደር እና የአዲስ ኢንተርናሽናል ኮንቬንሽንና ኤግዚቢሽን ማዕከል ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 10.8 ኪ.ሜ)
4. ሳር ቤት- ካርል አደባባይ- ብስራተ ገብርኤል- አቦ ማዞሪያ- ላፍቶ አደባባይ- ሃና ፉሪ ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 15.9 ኪ.ሜ)
5. አንበሳ ጋራዥ- ጃክሮስ- ጎሮ ኮሪደር ( የኮሪደሩ ርዝመት 3.1 ኪ.ሜ)
6. አራት ኪሎ- ሽሮ ሜዳ- እንጦጦ ማርያም- እጽዋት ማዕከል ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 13.19 ኪ.ሜ)
7. ቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 20 ኪ.ሜ)
8. እንጦጦ-ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ ኮሪደር (የኮሪደሩ ርዝመት 21.5 ኪ.ሜ)
ከላይ የተዘረዘሩ ኮሪደሮችን ምዕራፍ በምዕራፍ ከፍለን በጥራት እና በፍጥነት የምንሰራ ሲሆን፣ የከተማችን ነዋሪዎች እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ የትራፊክ መጨናነቅን ጨምሮ የሚኖሩ ምቹ ያልሆኑ ሁኔታዎችን በመቻል እንደ መጀመሪያው ዙር በትብብር ከተማችንን በጋራ እንድንገነባ አደራ እላለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.