የ6ኛው የሚላን የምገባ ፎረም ተሳታፊዎች በደጃዝማች ወንድይራድ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና በተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከላት ጉብኝት አካሄዱ።
ጉብኝቱ በዋናነት በትምህርት ቤቱ እየተተገበረ የሚገኘውን የተማሪዎች የምገባ አገልግሎት እና በቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም የተከናወኑ ተግባራትን መሰረት አድርጎ መካሄዱን የመርሀግብሩ አስተባባሪዎች አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ዘላለም ሙላቱ ከተማ አስተዳደሩ ትኩረት አድርጎ ከሚንቀሳቀስባቸው ዘርፎች አንዱ የቀዳማይ ልጅነት ፕሮግራም መሆኑን ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች ገለጻ ባደረጉበት ወቅት ጠቁመው ደጃዝማች ወንድይራድ ቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፕሮግራሙ ተግባራዊ ተደርጎባቸው ትራንስፎርም ከሆኑ ተቋማት አንዱ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ዶ/ር ዘላለም ገለጻቸውን በመቀጠል የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ለቀጣዩ የትምህርት ደረጃ መሰረት የሚጣልበት እንደመሆኑ ትምህርት ቤቶቹ ለህጻናቱ ጫወታን መሰረት ያደረገ የትምህርት አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ በከፍተኛ በጀት የግብአት ድጋፍ መደረጉን አመላክተዋል።
ከትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም ጋር በተገናኘ በ2017 ዓ.ም ከ824ሺ በላይ ተማሪዎች በቀን 2ጊዜ እየተመገቡ እንደሚገኙ ዶ/ር ዘላለም ገልጸው የምገባ መርሀ ግብሩ የተማሪዎችን መጠነ ማቋረጥ እንዲቀንስ ከማድረጉ ባሻገር በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ያበረከተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል።
የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በትምህርት ቤቱም ሆነ በተስፋ ብርሀን የምገባ ማዕከላት ባደረጉት ምልከታ በኢትዮጵያ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ መሆን የሚያስችል መሆኑን አስታውቀዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.