በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ በሃገራችን ለ2...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ21ኛ ጊዜ በሃገራችን ለ20 ኛ ጊዜ የፀረ ሙስና ቀን በዓልን አስመልክቶ "ስነምግባራዊ ትዉልድ ለሁለንታዊ ብልፅግና" በሚል መሪ ቃል የፖናል ዉይይት ተካሔደ።

ዉይይቱ በአዲስ አበባ ስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ፣በአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ እና በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የጋራ ቅንጅት የተዘጋጀ ነዉ ተብሏል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የሠላም የፍትህና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ሙሉነህ ደሳለኝ እንደገለፁት ሙስና ትልቅና ሠፊ አጀንዳ የያዘ እንደሀገርም ሌብነትና ብልሹ አሰራር በማህበራዊ በኢኮኖሚና በፖለቲካዊ ለምናደርገዉ ጉዞ ትልቅ ስብራት መሆኑን ጠቅሰዉ ጉዳዩን የራሳችን እንጂ ለሌላ የሚተዉ ያለመሆኑ ይህ ዉይይት ማሳያ ነዉ ብለዋል።

አክለዉም ለበርካታ ዓመታት በከተማ አስተዳር መዋቅር ዉስጥ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ያልተቋቋመ እንደነበረ ገልፀዉ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ተቋሙ ህጋዊ እዉቅና ተሰጥቶት ወደ ተግባር መግባቱን ጭምር ገልፀዉ በተደረገዉ ክትተልና ድጋፍ 41 ተቋማት ላይ ጥናት በማድረግ ለሙስና ተጋላጭ የሆኑና ክፍተት ያለባቸዉ ተለይተዉ በ16 ተቋማት ላይ በተወሰደዉ እርምጃ መሻሻሎች መታየቱና በከተማዋ በትምህርት ተቋማት አስተሳሰብና ልማት ላይ በመስራት በርካታ ለዉጦች እየተመዘገበ መሆኑና ሚዲያዎችም ጅምርና ተስፋ ሰጪ ስራዎችን እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጀማል ረዲ በበኩላቸዉ ሙስና ሀብትና ንብረት የሚጎዳ ብቻ ሳይሆን የትዉልድ ነፃነትን የሚገፍና ትዉልዱ ማግኘት የሚገባዉን የሚያሳጣ በሀገራት የሚታይ መገለጫ መሆኑን ጠቅሰዉ ይህን ከፊት ሆኖ ለመታገልና ለመግታት ሌላዉንም ለማታገል የወጣቱ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ከዚህ ዉይይት ልምድና ተሞክሮ በመዉሠድ የትዉልዱን አቅምና የተዘረጉ አሰራሮችን እንዲሁም መረጃን እንደሀብት በመጠቀም ሀገርና ትዉልድን ወደ ተሻለ ማሻገር ከሁሉም ማህበረሰብ የሚጠበቅ ነዉ ሲሉ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ዋና ኃላፊ አቶ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው ህዝባዊ ፋይዳ ባላቸዉ ሀገራዊ እና ቀጠናዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት በማድረግ መረጃን ለሀገር ዉስጥና ለተቀረዉ አለም ተደራሽ ከማድረግ በርካታ ስራዎችን በመስራት ኃላፊነቱን አየተወጣ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ገልፀዉ የዛሬዉም መርሀ ግብር ተቋሙ ሲሳተፍ የሀገራችን ብሎም የመዲናችንን የእድገት ፍላጎት እና ትልም ለማሳካት ትላልቅ እድሎች ያሉን በመሆኑ በትዉልዱ ላይ ይህን እዉን ለማድረግ ሁላችንም የበኩላችንን ልንወጣ ይገባል ብለዋል።

ለውይይት ሶስት እርእሰ ጉዳዮች የቀረቡ ሲሆን በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚንስተር ዲዔታ በሆኑት ምህረቱ ሻንቆ(ዶ/ር) በትዉልድ ግንባታ፤የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ በወ/ሮ እናትአለም መለሰ ስነምግባራዊ ትዉልድ በመፍጠር ሂደት የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ድርሻ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስነምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር በመቅደስ ተስፋዬ በስነምግባር የታነፀ ሙስናን የሚፀየፍ ትዉልድ ለሀገር ግንባታ ያለዉ ድርሻ ላይ ዉይይት ተደርጎባቸዉ ለቀጣይ ስራ ግብዓት መወሰዱ ተመላክቷል ፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.