" የዜጎች ተጠቃሚነትና የኑሮ መሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት የሚፈልግና መዘናጋትን የማይፈቅድ መሆኑን በመረዳት በቀጣይም በልዩ ትኩረት ይመራል" - አቶ ሞገስ ባልቻ
በየደረጃው የሚገኙ አመራሮች ያለፉትን አምስት ወራት በተለይም የሶስት ወራት የንቅናቄ ስራ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ያሉትን የስራ ዕድል ፈጠራ እና የሌማት ቱሩፋት ተግባራት አፈፃፀም የሚገኝበትን ሁኔታ ገምግመዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ /ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በግምገማዊ ውይይቱ ላይ እንደተናገሩት በተለይም የሶስት ወር የንቅናቄ ዕቅድ ከመጀመሩ በፊት በአንዳንድ ተቋማት የነበረው ዝቃ ያለ አፈፃፀም ወደ ኋላ ቢጎትትም በህዳር ወር አበረታች ስኬት መመዝገቡን ገልፀዋል።
ከፀጋ ልየታ እስከ ስራ ዕድል ፈጠራ ያሉት ተግባራት ተያያዥ በመሆናቸው ተናባቢና ወጥነት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል ያሉት አቶ ሞገስ አመራር የሰጠው ትኩረት እና በየደረጃው የነበረው የክትትልና ድጋፍ አግባብ በአፈፃፀም ላይ ልዩነት መፍጠሩን አመላክተዋል ።
የዜጎች ተጠቃሚነትና የኑሮ መሻሻል ጉዳይ ከፍተኛ ትኩረት የሚፈልግና መዘናጋትን የማይፈቅድ መሆኑን በመረዳት በቀጣይም በልዩ ትኩረት እንደሚመራ የገለፁት አቶ ሞገስ በቅርቡ መሬት ላይ ያለውን ተጨባጭ ስራ ለመመልከት የሱፐርቪዥን ስራ እንደሚካሄድም ገልፀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጥራቱ በየነ የስራ ዕድል ፈጠራ እና የሌማት ቱሩፋት ውጤታማነት ተቋማት ተቀናጅተው ህዝብን አስተባብረው የሚያስመዘግቡት ስኬት መሆኑን ጠቅሰው ባለፉት ወራት በመንግስት እና በፓርቲ የተቀናጀ ጥረት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን ገልፀው ወደኋላ የቀሩ ተቋማት ክፍተቶቻቸውን ፈጥነው እንዲያርሙ አሳስበዋል።
ኢንተርፕራይዞችን በዘመናዊ የመረጃ አያያዝ ዘዴ ለመመዝገበ የተጀመረው ተግባር ቬዶችን አላግባብ የሚይዙ ግለሰቦች እንዳይኖሩ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የጠቆሙት ኃላፊው የሌማት ቱሩፋትን የስራ ዕድል የመፍጠር ፀጋም በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል።
ባለፉት ወራቶች በግንዛቤ ፈጠራው ፣ በምዝገባ ፣ በስልጠና ፣ ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት እና በመሳሰሉት የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት እንዲሁም ከተማችን ለሌማት ቱሩፋት ያሏትን ዕምቅ አቅሞች በአግባቡ ጥቅም ላይ ለማዋል የተደረጉ ርብርቦች ውጤታማ እንደነበሩ ተመላክቷል።
በተለያዩ መመዘኛዎች እኩል መራመድ ያልቻሉ ተቋማት ግምገማቸውን ወስደው በሀላፊነትና በተጠያቂነት ስሜት እንደሚረባረቡ አረጋግጠዋል።
አቶ ሞገስ ባልቻ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.