በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማኅበራዊ ትረስ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የማኅበራዊ ትረስት ፈንድ ጽ/ቤት ችግረኛ ወገኖችን ለመርዳትና በዘላቂነት ለማቋቋም በሚያደርገው ጥረት ማኅበራዊ ሓላፊነታቸውን እየተወጡ ያሉ የአፍሪካ ኅብረት አመራርና ሠራተኞች በከተማ አስተዳደሩ ሲሠሩ የነበሩ የልማትና ሰው ተኮር ተግባራትን ተዘዋውረው ጎበኙ፡፡

የአመራርና ሠራተኛ አባላቱ ጉብኘት ያደረጉት በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን ለነገዋ የሴቶች ተሐድሶና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል፣ የልደታ ክፍለ ከተማ የተስፋ ብርሃን የምገባ ማእከል፣ የአድዋ ድል መታሰቢያና በከተማዋ የተሠሩ የተለያዩ የኮሪደር ልማቶችን ነው፡፡

አባላቱ ከጉብኝት በኋላ በሰጡት አስተያየት በከተማዋ እየተስተዋሉ ያሉት ልማቶች አበረታችና ዓለምአቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ናቸው፡፡ በተለይ የነገዋ የሴቶች የልህቀት ማእከል በተለያዩ ምክንያት የአካልና የሥነ-ልቡና ጉዳት የሚደርስባቸው ሴቶች የሚያገግሙበትና በተለያዩ የሙያ ዘርፍ ሠልጥነው ወደ ሥራ የሚሰማሩበት በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡

አያይዘውም ሁላችንም ለዚህ በጐ ተግባር አሻራችንን ማሳረፍ ይጠበቃል፤ ተግባሩም ትልቅ የመንፈስ እርካታ የሚያስገኝና ነፍስን የሚያስደስት፤ መደጋገፍንና መረዳዳትን የሚያጐለብት ነው፡፡ በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋም ማካፈልን እንደ ባህል በመቁጠር ማኅበራዊ ሓላፊነቱን ሊወጣ ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡

ሌላው የጉብኝት አካል የሆነው የልደታ የተስፋ ብርሃን ምገባ ማእከል ሲሆን በዚህም አባላቱ በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ የማይችሉ የከተማ ነዋሪ ወገኖችን በማእከሉ በመገኘት ምሳ የማብላት መርሐ ግብር አካሒደዋል፡፡

በዚሁ ጊዜ በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች የምገባ ማእከላትን በመገንባት ከ36,500 በላይ የሚሆኑ በቀን አንድ ጊዜ መመገብ የማይችሉ ዜጎች እንደሚመገቡ ተገልጾ ለዚህ ሰናይ ተግባር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ማኅበራዊ ሓላፊነቱን እንዲወጣና ድጋፍ እንዲያደርግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ማኅበራዊ ትረስት ፈንድ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ አሥራት ንጉሴ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት አመራርና ሠራተኞች ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ሳያቋርጡ ማኅበራዊ ሓላፊታቸውን እየተወጡ ያሉ በመሆናቸው ወ/ሮ አሥራት የላቀ ምስጋና አቅርበው፤ ድጋፍ በገንዘብ ብቻ ሳይሆን ባለን አቅም በዕውቀት፣ በአገልግሎት፣ በሙያ፣ በዓይነትና በማገዝ ጭምር ማኅበራዊ ሓላፊነታችንን ከተወጣን በከተማችን ማኅበራዊ ፍትሕን ማረጋገጥ እንችላለን ሲሉ አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም የአፍሪካ ኅብረት አመራርና ሠራተኞች ማእከላቱንና በከተማዋ የተሠሩ የተለያዩ የኮሪደር ልማቶችን ከመጎብኘታቸው ባሻገር የኢትዮጵያውያን ብሎም የአፍሪካውያን የድል ኩራት የሆነውን የአድዋ ድል መታሰቢያ በመጎብኘት መርሐ ግብሩ ተጠናቋል፡፡

 

 

 

 

 


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.