ለህብረተሰባችን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ለህብረተሰባችን ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የኑሮ ጫና ከማቃለልና ገበያ ለማረጋጋት ላበረከቱት አስተዋፅኦ የንግዱን ማህበረሰብ እናመሰግናለን" አቶ ጃንጥራር አባይ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ይህንን ያሉት በዛሬው እለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ “ምርት አቅርቦት ለገበያ ማረጋጋት!” በሚል መሪ ቃል ባለፉት አመታት ለገበያ መረጋጋቱ ትልቅ አስተዋጽዎ ላበረክቱ አምራችና አቅራቢዎች እንዲሁም ለሴክተር ተቋማት የእዉቅና ሽልማት መድረክ በኢሊሊ ሆቴል በክብር እንግድነት በተዘጋጀው መድረክ ላይ ነው።

አምራቾች ፣ ጅምላ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ከከተማ አሰተዳደሩ ጎን በመቆም በእህል ሰብል ምርት ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም በእንዱስትሪ ምርቶች ለህብረተሰባችን ሰፊ ምርት በማቅረብና በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥ የኑሮ ጫና ከማቃለልና የገበያ መረጋጋት በመፍጠር በኩል ለአደረጋችሁት አስተዋፅኦ በከተማ አስተዳዳሩ ፣ በንግድ ቢሮ እንዲሁም በራሴ በስሜ ከልብ አመሠግናችኋለሁ ብለዋል ም/ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ ።

አክለዉም የገበያ ቦታዎችን በማደራጀትና በማዘመን እንዲሁም በኢትዮጵያ ታምርት ምርት ወደ ገበያ በሰፊዉ እንዲገባ ና አምራች በቀጥታ ለሸማቹ በዘለቄታዊ መልኩ እንዲያቀርብ ከግብረ ሀይሉ ጋር በምንሰራቸዉ ስራዎች በቀጣይም በፍትሀዊነት እንድትወጡ አደራ በማለት መልዕክታቸዉን እውቅናና ምስጋና ለቀረበላቸው ባለ ድርሻ አካላት አስተላልፈዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በበኩላቸው ቢሮዉ በተሠጠዉ ስልጣንና አዋጅ ቁጥር 84/2016 መሠረት የነዋሪዉን ኑሮ ዉድነትን በመቀነስና አምራችና ሸማችን በቀጥታ በማገናኘት ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው መድረኩ ዉጤታማ ስራዎች መሰራት በመቻላቸውን እና በቀጣይም አጠናክሮ ለመቀጠል ያለመ የምስጋና መርሀ ግብር መሆኑን ገልፀዋል።

በ2014 በአምስት ቦታዎች የተጀመረዉ የቅዳሜና እሁድ ገበያ በአሁኑ ሰዓት በ11ዱም ክፍለ ከተሞች በ119 ወረዳዎች 197 የገበያ ስፍራዎች መድረሳቸዉን ጠቁመዋል።

በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ነጋዴዎች በንግድ ስርዓቱ መሳተፋቸውን ገልፀዉ ይህም ንግድ ቢሮዉ ከከተማ አስተዳደሩና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት በተሠራዉ ቅንጅታዊ ስራ ትልቅ ዉጤት የተመዘገበበት ነዉ ሲሉ የቢሮ ኃላፊዋ ተናግረዋል።

በተጨማሪም በእነዚህ 197 የገበያ ቦታዎች ላይ 126 ማህበራት ፣ 82 የከተማ ግብርና ፣19 አምራች ኢንዱስትሪ ፣ 282 ኢንተርፕራይዞች ፣ 1010 ጅምላ ቸርቻሪዎች በድምሩ 1852 ቀጥታ ትስስር የተፈጠረላቸዉ ተዋናዮች ተሳታፊ መሆናቸዉንም አመላክተዋል።

በተጠቀሱትም የገበያ ቦታዎች እስከአሁን ባከናወናቸው ተግባራት የነዋሪዉን ኑሮ በማቃለል ረገድ ምርት በሰፊዉ በማቅረብ ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ያለምንም የአቅርቦት ችግር በአላትን ጭምር ማሳለፍ ችለናል ብለዋል።

አሁንም በገና ዋዜማ በተሠራዉ ቅንጅታዊ ስራ በየትኛዉም የግብይት ቦታ ምርት በሰፊዉ የገባ በመሆኑ ምንም አይነት የምርት አቅርቦት እጥረት እንደሌለና ሸማቹም በተመጣጣኝ ዋጋ መሸመት እንደሚችልም ገልፀዋል።

በመድረኩ ላይ ቢሮዉ ለዉይይት ባዘጋጀው "የእሁድ ገበያ የኑሮ ዉድነትና የገበያ ዋጋን ለማረጋጋት የነበራቸዉ ፋይዳና የቀጣይ አቅጣጫ" በተመለከተ ሠነድ ቀርቦ ዉይይት በማድረግ ለቀጣይ ሥራ መሠረት የሚጥል ግብዓት መወሠድ መቻሉ ተገልጿል።

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ከክልል 10 የወረዳ ግብርና ፅ/ቤት ተወካይ አመራሮች ጋር የመግባቢያ ሠነድ ፊርማ ስነስረአት ተከናውኗል።

በመጨረሻም በእውቅና መድረኩ ላይ የከተማዋ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ፣ የክፍለ ከተማና የወረዳ አመራሮች የክልል የቢሮ ኃላፊዎች አምራችና አቅራቢዎች እንዲሁም ዩኒየን ማህበራትና የሸማች ህብረተሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።

ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች

https://linktr.ee/addisababacommunication


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.