የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በከተ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ በከተማው የነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭትና የቁጥጥር ሂደቶች ላይ መግለጫ ሰጠ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ለአዲስ አበባ ከተማ እየቀረበ ባለው ነዳጅ አቅርቦት፣ ስርጭት እና ቁጥጥር ሂደትን በሚመለከት ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራ አንስቶ ልዩ የክትትል እና ድጋፍ ስርዓት በመዘርጋቱን ይፋ አድርጓል።

በዚህም በከተማዋ 125 ማደያዎች ቀርቦ በመሰራጨት ላይ ያለ የነዳጅ ምርት መጠን በሊትር ናፍጣ በአማካኝ በቀን 2.0 ሚሊዮን ፣ ቤንዚን በአማካኝ በቀን 1.45 ሚሊዮን ሊትር በድምሩ ባለፉት ስድስት ወራት በቀን በአማካኝ 3.45 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ በበቂ መጠን መቅረቡን አመላክተዋል፡፡

ለፕሮጀክቶች እና ነዳጅ ለሚጠቀሙ ለተፈቀደላቸው 234 ተቋማትም አሰራሩን በጠበቀ አግባብ ናፍጣ 1,047,422 እና ቤንዚን 978,071 በድምሩ 2,025,493 ሊትር ነዳጅ ለተቋማቱ መሰራጨቱን የቢሮ ሀላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ጠቅሰዋል፡፡

በቁጥጥር ሂደት ህገ-ወጥ ተግባር ውስጥ የገቡ ነዳጅ ማደያዎች ላይም እርምጃ መወሰዱን ያስታወሱት የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ በዚህም በህገ-ወጥ ሲዘዋወር የተወረሰ የነዳጅ መጠን ቤንዚን 18985 ሊትር፣ ናፍጣ 9434.5 እና ነጭ ጋዝ 189 በድምሩ 28608.5 ሊትር ነዳጅ መወረሱን እና የዋጋ ጭማሪ በመጠባበቅ ሳይሰራጭ የቆየ አንድ ቦቲ ቤንዚን የዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ በመደበኛው ገበያ 19000 ሊትር እንዲሸጥ በማድረግ ጭማሪው ለመንግስት ገቢ እንዲሆን ተደርጓል ብለዋል፡፡ በጥቅሉም 47608.5 ሊትር ነዳጅ ምርቱ ተሽጦ 2,600,649.94 ብር ለመንግስት ገቢ መደረጉም በመግለጫቸው አውስተዋል፡፡

በቀጣይም ቢሮው የነዳጅ አቅርቦትና ስርጭቱን ጤናማ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ አበክሮ እንደሚሰራ የገለጹት ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ቢሮው በፍጹም የማይታገሳቸውንና በህጉ መሰረት ጠበቅ ያለ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደድባቸውንም ነጥቦች አብራርተዋል ። ለአብነት ነዳጅን በኮንትሮባንድ በመሸጥ ከከተማ እንዲወጣ የሚያደርጉ ማደያዎችን ፣ ከኤሌክተሮኒክስ የመገበያያ አማራጮች ውጪ ነዳጅን በጥሬ ገንዘብ ሽያጭ የሚፈጽሙ እንዲሁም በማደያቸው የሚገኙ ማሽኖችን ሁሉንም አገልግሎት ላይ ባለማዋል ተገቢ ያልሆነ ሰልፎችን የሚፈጥሩትንና በመጨረሻም በንግድ ፍቃድ አሰጣጥ መስፈርቱ ላይ በተቀመጠው መሰረት የ24 ሰዓት አገልግሎት በማይሰጡ ማደያዎች ላይ በህጉ በተቀመጠው አግባብ እርምጃዎችን እንደሚወስድ አሳስበዋል፡፡

በመግለጫቸው ማጠቃለያም ማደያዎች በመንግስት የሚቀርበውን ነዳጅ ስርዓቱን በጠበቀና በህጋዊ አግባብ ማሰራጨት እንደሚገባቸውና ማህበረሰቡም ይህን አውቆ አገልግሎቱን በፍትሀዊነት ማግኘት እንዲችል ሁሉም ባለድርሻ አካላት በቅንጅት መስራት እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.