ለከተማችን ትልቅ የምስራች እነሆ! የከንቲባ አዳነች አቤቤ መልዕክት
ለከተማችን ትልቅ የምስራች እነሆ!
በ100 ሺህ ካሬ ሜትር ስፍራ ላይ ያረፈው የሴቶች የተሀድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል ለአገልግሎት ክፍት ይደረጋል።
ማዕከሉ በዋነኛነት በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶችን በመቀበል ሙያዊ እና ስነ ልቦናዊ ድጋፍ፣ ክትትልና ስልጠናዎችን እንዲያገኙ በማድረግ ወደ ስራ እንዲሰማሩ የሚያደርግ ሲሆን፣ በአንድ ዙር ብቻ 10,000 ሴቶችን ተቀብሎ የማሰልጠን አቅም አለው።
ወጣት ሴቶቹ በማዕከሉ ቆይታቸው ከሚያገኙት የስነ ልቦና ድጋፍ በተጨማሪ በስነ-ውበት፣ በከተማ ግብርና ፣ በምግብ ዝግጅት፣ በከተማ ውበት አጠባበቅ፣ በኮምፒዩተር ሙያ፣ በሞግዚትነት፣ በመስተንግዶ፣ በፀጉር ስራ፣ በኤሌክትሪክና ሸክላ ስራ፣ በእንጨት ስራዎች፣ በልብስ ስፌት እንዲሁም በሌሎች የሙያ ዘርፎች በቂ ስልጠና በመስጠት ወደ ስራ እንዲገቡ የምናደርግ ይሆናል።
ከዚህም በተጨማሪ ማዕከሉ ምቹ የመኝታ ክፍሎች፣ ቤተ-መጻህፍት፣ የቤት ውስጥ ስፖርት ማዘውተሪያ ጂምናዚየም፣ ምቹ የመመገቢያ አዳራሾች፣ ዘመናዊ የምግብ ማብሰያ፣ በመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አቅም የተደራጀ ዘመናዊ የህክምና ማዕከል፣ የተግባራዊ ልምምድና የሰርቶ ማሳያ ማዕከላት፣ የልብስ ንጽህና መጠበቂያ ላውንደሪዎች፣ የህጻናት ማቆያና እንክብካቤ ማዕከላት፣ የህጻናት ስነ-አዕምሮአዊ እድገት ክትትልና ልህቀት ክፍል እንዲሁም የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎች የተካተቱበት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው።
ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት ከተማን ለመገንባት ለህዝባችን የገባነውን ቃል እየፈጸምን አሁንም የመረጠንን ህዝብ በታማኝነትና በትጋት ማገልገላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን!
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ!
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.