የጥምቀት በዓል የህዝቦችን ትስስር በማጠናከር ፣ቱሪዝምን በማሳደግ እና ከተሞችን በማነቃቃት ረገድ ትልቅ ሚና አለው፡-አቶ ጃንጥራር አባይ
የጥምቀት በዓል የህዝቦችን ትስስር በማጠናከር ፣ቱሪዝምን በማሳደግ እና ከተሞችን በማነቃቃት ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡
የጥምቀት በዓል በጃን ሜዳ በድምቀት ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ መልእክት ያስተላለፉት አቶ ጃንጥራር አባይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጥምቀት በዓል ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በየዓመቱ በድምቀት እንዲከበር ከሀይማኖት አባቶች ጋር እየሰራ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የጥምቀት በዓል በተመድ የትምህርት፣የሳይንስ እና የባህል ድርጅት ዩኔስኮ በማይዳሰሱ የዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ታላቅ በዓል መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
በዓሉ በአዲስ አበባም ሆነ በመላው ሀገሪቱ ከዳር እስከ ዳር በታላቅ ድምቀት እየተከበረ እንዳለም አውስተዋል፡፡
አዲስ አበባ ህብረ ብሄራዊ ከተማ እንደመሆኗ የሀይማኖቶች ልዩነት እና ገደብ ሳይኖር ሁሉም በእኩል የሚስተናገዱባት ከተማ መሆኗም ገልጸዋል፡፡
በዓሉ በከተማዋ በሁሉም አድባራት ባማረ እና በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ እንደሚገኝም አውስተዋል፡፡
በዓሉ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ በዓል እንደመሆኑ ከተለያዩ ዓለማት የመጡ ቱሪስቶች እና ጎብኚዎች መታደማቸውንም አቶ ጃንጥራር ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የኢትዮጵያን እና የአዲስ አበባን ገጽታ ከፍ በማድረግ ረገድ ሁሉም ዜጋ የአምባሳደርነት ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
ምክትል ከንቲባው በዓሉ በድምቀት እንዲሁም ሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ትውፊቱን ጠብቆ ባማረና በደመቀ ሁኔታ እንዲከበር ላደረጉ የሀይማኖት አባቶች ፣ወጣቶች፣ የጸጥታ ሐይሎችና የከተማዋ ነዋሪዎች ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.