በሲቪል ምዝገባ እና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የሚሰሩ የሪፎርም ስራዎች መዲናዋን ስማርት ለማድረግ ከፍተኛ ድርሻ አላቸው- ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ
በሲቪል ምዝገባ እና ነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ የሚሰሩ የሪፎርም ስራዎች አዲስ አበባ ከተማን ስማርት ከተማ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳላቸው በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ተናገሩ።
የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ መደበኛ የሰራተኛ ደንብ ልብስ ማልበስ ስነ- ስርዓት እና ሁለተኛውን የእውቅና መርሃ ግብር አካሂዷል።
81 አመታትን ያስቆጠረው ተቋሙ ከአገልግሎት አሰጣጡ ጋር በተያያዘ በርካታ ቅሬታዎች ሲቀርቡበት እንደነበረ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ዮናስ አለማየሁ ተናግረው ባለፉት ሁለት አመታት ተኩል በተሰራው የሪፎርም ስራ በርካታ መሻሻሎች መምጣታቸውን ገልጸዋል።
በቴክኖሎጂ ፣ በአሰራር ፣ በሰው ሀብት፣ በአደረጃጀት እና የስራ ከባቢን ምቹ በማድረግ ላይ ያተኮረው የተቋሙ ሪፎርም ቀልጣፋና ከብልሹ አሰራር የጸዳ አገልግሎትን ለመስጠት መሰረት እንደጣለ ነው የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ። በዚህ አመት ሪፎርሙን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ወደ ተሟላ ትግበራ እንደሚገባም አስታውቀዋል።
የተቋሙ ሰራተኞች መደበኛ የደንብ ልብስ እንዲኖራቸው እና በየአመቱ የተሻለ አፈጻጸም ያላቸውን ሰራተኞች እውቅና መስጠትም የሪፎርሙ አካል መሆኑን ነው አቶ ዮናስ የገለጹት።
ከወረዳ እስከ ማዕከል ባለው የኤጀንሲው ተቋማት የተሻለ አፈጻጸም ላስመዘገቡ ሰራተኞች እውቅና የሰጡት በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ የከተማ አስተዳደሩ የጀመራቸው የሪፎርም ስራዎች እንዲሳኩ እያደረጉ ከሚገኙ ተቋማት አንዱ የሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ነው ብለዋል።
የተቋሙ አገልግሎት የከተማ አስተዳደሩ ለሚያከናውኗቸው ማናቸውም ስራዎች መሠረት ነው ያሉት ኢንጅነር ወንድሙ በተቋሙ የሚሰሩ የሪፎርም ስራዎች አዲስ አበባ ከተማን ስማርት ከተማ ለማድረግ የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ረገድ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለውም ተናግረዋል ።
የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች የተጀመረውን ሪፎርም ውጤታማ በማድረግ የተቀላጠፈ እና የተገልጋዩን እርካታ የሚያሳድግ አገልግሎትን በቀጣይነት እንዲሰጡም አሳስበዋል።
AMN
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.