
በተያዘው ሳምንት ለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ዓመታዊ የመሪዎች ጉባዔ ሁለንተናዊ ዝግጅት ተጠናቀቀ
በተያዘው ሳምንት ለሚካሄደው የአፍሪካ ህብረት ዓመታዊ የመሪዎች ጉባዔ ሁለንተናዊ ዝግጅት ተጠናቀቀ።
የጉባዔ ዝግጅት ሂደትን በተመለከተ የብሄራዊ ዝግጅት ዐቢይ ኮሚቴ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚቴው ሰብሳቢና የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ በጉባዔው ዝግጅት ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባዔ ዝግጅት የፌዴራል እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ተቋማትን ያቀፈ የጋራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ዝግጅት ሲያደርግ መቆየቱን ሚኒስትር ዴዔታዋ አውስተዋል።
ሁነቱ ለሀገር ብሄራዊ ጥቅምና ገፅታ ልዩ ትርጉም ያለው ሁነት ነው ያሉት አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አዲስ አበባ ዓለም አቀፍ ጉባዔ በስኬት የማስተናገድ ልምዷን ዳግም የምታፀናበት አጋጣሚ ነውም ብለዋል።
በዚህም ለዘንድሮ ጉባዔ በ 2 ዓብይና 35 ንዑሳን ኮሚቴ አባላት ሲደረግ የነበረው የጉባዔ ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
ብሄራዊ ዝግጅቱ የህብረቱ ስብሰባዎች በስኬት ማጠናቀቅ ፣ ብሄራዊ ጥቅሞችን ማስጠበቅ ፣ አዲስ አበባ አሁናዊ ልማትና ደረጃን ለእንግዶች ማስገንዘብ ፣ የኢትዮጵያን የቀደመ አፍሪካዊ አበርክቶና ድርሻ ዳግም ማፅናትን ዓላማ ያደረገ እንደሆነም ሚኒስትር ዴዔታዋ አብራርተዋል።
ለዚህም እንዲያግዝ ለዲፕሎማቶች ፣ ለፕሮቶኮል ካዴቶች ፣ ለሆቴል መስተንግዶ ባለሙያዎች ፣ ለአሽከርካሪዎች ፣ የኢሚግሬሽን አገልግሎት ሙያተኞች ፣ ለደህንነት አካላት ስልጠና ሲሰጥ ቆይቷልም ነው ያሉት ሚኒስትር ዴዔታዋ።
በተጨማሪም እንግዶቹን ለመቀበል፣ ለማስተናገድና ለማስጎብኘት በሶስት የውጭ ቋንቋዎች (እንግሊዝኛ፣ ፈረንሳይኛና አረብኛ) የፕሮቶኮልና የመስተንግዶ ባለሙያዎች ዝግጅት ተደርጓልም ነው ያሉት።
የዘንድሮው ጉባዔ ከእስካሁን ሁነቶች በተሻለ የደመቀ፣ የተሳካ እንዲሁም ሀገራዊ ገፅታ የሚገነባበትና ብሄራዊ ጥቅም የሚጠበቅበት ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሲደረግ የቆየው ዝግጅት መጠናቀቁን ሚኒስትር ዴዔታዋ አስታውቀዋል።
ከጉባዔው ባሻገርም የአዲስ አበባ ኮሪደር ልማት፣ የብሄራዊ ቤተመንግስት፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ ሀገራዊ የስበት ማዕከል የሆኑ ማዕከላትና የቱሪዝም መዳረሻዎችም ለጉብኝት ዝግጁ ሆነው እየተጠባበቁ መሆኑንም አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አስታውቀዋል።
ለዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት ጉባዔ አንድ ንጉስ ፣ 35 ርዕሳነ ብሄር እንዲሁም 19 ቀዳማዊ እመቤቶችን ጨምሮ ካለፈው ዓመት ከተመዘገበው ከፍ ባለ መጠን ከፍተኛ ቁጥር ያለው እንግዳ ይጠበቃል።
ሚኒስትር ዴዔታዋ መግለጫ እስከሰጡበት አፍታ ከ11 ሺ በላይ የጉባዔ ተሳታፊዎች ተመዝግበው ፈቃድ ተሰጥቷቸዋልም ተብሏል።
በመጪው የካቲት 5 እና 6 ቀን 45ኛው የአፍሪካ ህብረት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ እንዲሁም የካቲት 8 እና 9 ቀን 38ኛው የህብረቱ መሪዎች ጉባዔ ይካሄዳል።
AMN
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.