በህብረት ስራ ማህበራት ላይ የተጀመረው ሪፎርም ዘላቂነት ላለው ተጠቃሚነት የላቀ ድርሻ እንደሚኖረው ተመላከተ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ህብረት ስራ ማህበራት ኮሚሽን የተቋሙን ሪፎርም ስኬታማ ለማድረግ በየደረጃው ሲያካሂድ የነበረውን የማህበራት አመራሮች እና አባላት ውይይት በከተማ ደረጃ አጠቃሏል።
የአዲስ አበባ ከተማ ም / ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ የህብረት ስራ ማህበራት በከተማ ደረጃ ባደረጉት ውይይት እንደተናገሩት የከተማ አስተዳደሩ ማህበራቱ የኑሮ ውደነቱንና የዋጋ ንረቱን በማረጋጋት ለህዝባችን የሚያበረከቱትን አስተዋፅዖ በመረዳት የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
የህዝባችንን የኑሮ ጫና የማቃለል ተልዕኳቸውን ለመወጣት የተንቀሳቀሱ ህብረት ስራ ማህበራት ቢኖሩም ብክነቶች እና ጉድለቶች ስላሉ በሰው ሀይል፣ በአደረጃጀት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ለማጠናከር የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ /ፅ /ቤት ም/ሀላፊ እና የፖለቲካ ዘርፍ ሀላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ የህብረት ስራ ማህበራት ለህዝባችን የላቀ አገልግሎት ሊሰጡ ስለሚገባ የከተማ አስተዳደሩ የሚበጅተው የድጎማ በጀት ለህዝብ ጥቅም መዋሉን ለማረጋገጥ እና ህዝባችንን ከብዝበዛ ለመጠበቅ ድጋፍና ክትትሉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር ህብረት ስራ ማህበራት ኮሚሽን ኮሚሽነር ወ/ሮ ልዕልተ ግደይ የሪፎርሙ ዓላማ ጠንካራ ተቋም ለመገንባት መሆኑን ገልፀው ለስኬታማነቱም የህዝብ ሀሳብ መሰብሰቡን እና ጥናት መካሄዱን እንዲሁም በየደረጃው በተደረጉ ውይይቶች ተጨማሪ ግብአቶች መገኘታቸውን አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ከ110 ሺህ በላይ የህብረት ስራ ማህበራት ከ28 ሚሊየን በላይ ዜጎችን በአባልነት አቅፈው እንደሚገኙ እና በአዲስ አበባም ከ 9ሺህ 800 በላይ ህብረት ስራ ማህበራት እና ከ12 በላይ ዩኒየን እንደሚገኙ የኮሚሽኑ የፅ/ቤት ሀላፊ አቶ ይቻላል አይኔ ባቀረቡት የመወያያ ሰነድ ተጠቅሷል።
በከተማችን የሚገኙ ማህበራት ከ35ሺህ ለሚልቁ ዜጎችም የስራ ዕድል ፈጥረው እንደሚገኙ የተጠቀሰ ሲሆን የከተማ አስተዳደሩ ለህብረት ስራ ማህበራት 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉም ተመላክቷል።
በህብረት ስራ ማህበራቱ የሚስተዋለውን ያልዘመነ አገልግሎት ፣ የአሰራር ብልሽት እንዲሁም የአደረጃጀት ክፍተት ለማረም በኤጀንሲ ደረጃ የነበረውን ወደ ህብረት ስራ ኮሚሽን ማሳደግን ጨምሮ አዳዲስ መመሪያዎችን የማውጣትና የማሻሻል ስራ መከናወኑ በውይይቱ የተብራራ ሲሆን በየወረዳው እና በየክ/ከተማው በተደረጉ ውይይቶች በሪፎርሙ አስፈላጊነት ላይ መግባባት ላይ መደረሱም ተገልጿል::
የሰራተኞች ቅጥር ከዕውቀት እና ከስነ -ምግባር አንፃር እንዲሆን ፣ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን ፣ የሀብት ብክነትን፣ ሌብትንና ብልሹ አሰራርን ለማረም እንዲሁም የህግ ተጠያቂነትን ለማስፈን ከአባላቱ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ እና መንግስትም የሚጠበቅበትን የድጋፍና ክትትል ሀላፊነት እንደሚወጣ በውይይቱ ላይ ተገልጿል::
መንግስት ሪፎርሙን ስኬታማ በማድረግ የህብረት ስራ ማህበራት አቅም እንዲዳብርና አሰራራቸው እንዲዘምን ብልሽቶችም እንዲታረሙ ለሚያደርገው ጥረት የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንደሚወጡ የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.