10ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎችና መምህራን የስፖ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

10ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎችና መምህራን የስፖርት ሊግ ውድድር የመክፈቻ መርሀ ግብር በአዲስ አበባ ስቴዲየም በድምቀት በዛሬው እለት ተጀመረ።

ስፖርታዊ ውድድሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮና ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በጋራ "የትምህርት ቤቶች ስፖርት ሊግ ውድድርን ባህል በማድረግ ጤናማ ንቁና ብቁ ትውልድ እንፈጥራለን" በሚል መሪ ቃል የሚካሄድ ሲሆን የመክፈቻ መርሀ ግብሩ  ተማሪዎች፣ መምህራን ፣ወላጆች ፣የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎችን ጨምሮ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው አካላት በተገኙበት በአዲስ አበባ ስቴዲየም በድምቀት ተካሂዷል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የመክፈቻ መርሀግብሩ የክብር እንግዳ አቶ ሞገስ ባልቻ  ባስተላለፉት መልዕክት ትምህርት ለአንድ ሀገር ሁለንተናዊ እድገትና ብልጽግና መሰረት እንደመሆኑ ከተማ አስተዳደሩ ለትምህርት ሴክተሩ ውጤታማነት የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ላይ እንደሚገኝ ጠቁመው የተማሪዎችና የመምህራን ስፖት ሊግ ውድድር ብቁና ንቁ ትውልድ ከመፍጠር እረገድ ከፍተኛ ሚና የሚጫወት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የከተማ አስተዳደሩም እያከናወናቸዉ የሚገኙ የልማት ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ የትምህርት ማህበራሰቡ አካላት የሚናቸዉን እንዲወጡ አደራ ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ዘላለም ሙላቱ በስፖርታዊ ውድድሩ የመክፈቻ መርሀግብር ባስተላለፉት መልዕክት በተማሪዎች እንዲሁም በመምህራን መካከል የሚካሄደዉ ስፖርታዊ ውድድ የተማሪዎችን የታመቀ አቅም በማውጣት በሀገር አቀፍና አለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ስፖርተኞችን ከማፍራቱ ባሻገር በአካልና አዕምሮ ዳብረው በትምህርታቸው ውጤታማ የሆኑ ዜጎችን ለመፍጠር በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመው 10ኛው ከተማ አቀፍ የተማሪዎችና መምህራን የስፖርት ሊግ ውድድር የመክፈቻ ፕሮግራም በድምቀት እንዲካሄድ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን በበኩላቸው ትምህርት ቤቶች የወደፊት የሀገር ተረካቢ ዜጎች የሚፈሩባቸው ተቋማት ከመሆናቸው ባሻገር ተተኪ ምርጥ ስፖርተኞች የሚወጡባቸው ስፍራዎች መሆናቸውን ገልጸው የስፖርት ሊግ ውድድሩ እስከ ሚያዝያ 4/2017ዓ.ም ድረስ በተለያዩ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንደሚካሄድ ተናግረዋል፡፡

ስፖርታዊ ውድድሩ  በአትሌቲክስ፣በጠረጴዛ ቴኒስ፣በቼዝ፣በቅርጫት ኳስ፣በመረብ ኳስ ፣በእግር ኳስ፣በእጅ ኳስ፣በውሀ ዋና፣በባህል ስፖርቶች፣በገመድ ጉተታ እንዲሁም የፓራሌምፒክ የውድድር አይነቶች በተማሪዎች እና በመምህራን መካከል ከትምህርት ሰአት ውጭ የሚካሄድ ይሆናል፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.