
ዛሬ የየካቲት 12 ሆስፒታል ሜዲካል ኮሌጅ በህክምና ሳይንስ እና በጤና ሳይንስ ያስተማራቸውን 186 የህክምና ባለሙያዎች አስመርቀናል። ተመራቂዎች እንኳን ደስ አላችሁ !
መንግስት ያወጣውን በሽታን የመከላከል እና አክሞ የማዳን ፖሊሲ ለመተግበር ግልጽና ቁልፍ መለኪያዎችን አውጥተን በርካታ ስራዎችን በመስራት ላይ እንገኛለን።
በሽታን ከመከላከል እና ጤናማ ማህበረሰብ ከማፍራት አንጻር ከተማችንን ጽዱ፣ ውብ፣ ለነዋሪዎች ምቹ እንዲሁም ከብክለት የጸዳ አካባቢ እንዲሆን ለማድረግ ሰፋፊ ስራዎች ተሰርተዋል።
አክሞ በማዳን ነዋሪዎች ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ እና ከተማችንን የጤና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የጀመርነውን እቅድ ከግብ ለማድረስ የኮልፌ እና የላፍቶ ሪፈራል ሆስፒታሎችን ግንባታ በማጠናቀቅ ላይ የምንገኝ ሲሆን ወቅቱን የዋጀ አገልግሎት እንዲሰጡ ዘውዲቱ፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ፣ ዳግማዊ ሚኒሊክ እና ራስ ደስታ ሆስፒታሎች ላይ ሰፋፊ የማስፋፊያ ስራዎችን እየሰራን ነዉ።
እነዚህ ሁሉ ስራዎች የታለመዉን ዉጤት የሚያስገኙት በዘርፋ የሰለጠኑ ብቁ የጤና ባለሙያዎች ሲሟሉላቸዉ በመሆኑ ዛሬ በህክምና ሳይንስ እና በጤና ሳይንስ ዘርፍ የተመረቃችሁ የጤና ባለሙያዎች በሙሉ ሙያችሁ በሚጠይቀው ስነ ምግባር ልክ በቅንነት፣ በታማኝነት እና በትህትና ህዝባችሁን እንድታገለግሉ አደራ ማለት እወዳለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን እና ህዝቦቿን ይባርክ
ከንቲባ አዳነች አቤቤ
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.