
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ በሰላም መንገድ ልማት ፕሮጀክት ምክንያት የልማት ተነሺ የሆኑ የቂርቆስ ወረዳ 01 ነዋሪዎችን አወያዩ
ውይይቱን ከአቶ ጥላሁን በተጨማሪ የክፍለ ከተማው ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደፍርስ ኮራ የመሩት ሲሆን የውይይቱ ዋና ዓላማ ከኡራኤል ወሎ ሰፈር አደባባይ ድረስ ያለውን አዲሱን የሰላም መንገድ በዘመናዊ መልኩ ማልማት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ተብሏል።
በከተማ አስተዳደሩ የሚካሄደው ልማት ህዝብን ከመንግስት ጋር በሚነጥል መልኩ የሚሰራ ባለመሆኑ ከተነሺ ነዋሪዎቹ ጋር መመካከር እንዲያስችል መድረኩ መዘጋጀቱን ውይይቱን የመሩት የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ወርቁ ተናግረዋል።
የከተማው ልማት ከእናንተ ከነዋሪዎች ጋር በመመካከር የሚሰራ ነው ያሉት አቶ ጥላሁን የከተማ አስተዳደሩ እንደከዚህቀደሙ ሁሉ የእናንተን አስፈላጊ ጥያቄ በመመለስ ቦታውን ለልማት ዝግጁ ያደርጋል ብለዋል።
በዛሬው እለት የተወያያችሁት የልማት ተነሺዎች በሰላም መንገድ አልሚዎች ምክንያት የምትነሱ ሲሆን ከዚህ በፊት የተጀመረውን ምትክ ቦታና ቤት የመስጠት ተግባር አጠናቀን በፍቃደኝነትና በምክክር ቦታውን የምትለቁ ይሆናል። ለልማቱ ስኬት እያሳያችሁ ላላችሁት ቀና ትብብር ከተማ አስተዳደሩ ምስጋና ያቀርብላችኋል ብለዋል አቶ ጥላሁን በውይይቱ ወቅት
የክፍለ ከተማው ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደፍርስ ኮራ በበኩላቸው የመንግስት ዋና ዓላማ የህዝቡን ብልፅግና ማረጋገጥ ነው።ይህንን ደግሞ በገባው ቃል መሰረት ለመፈፀሙ እናንተም ምስክር ናችሁ ። ሁሌም ለምታሳዩት ትብብር እናመሰግናለን ብለዋል።
ተወያዮቹም የከተማ አስተዳደሩ ህዝብን አክብሮ ለማወያየት በሩን በመክፈቱ አመስግነው ልማትን እንደግፋለን ነገር ግን ጥያቄያችንና የምንስተናገድበት አግባብ እስካሁን ጥሩ ነው። በቀጣይም ህግና አሰራሩን ተከትሎ ይተገበርልን ዘንድ እንጠይቃለን ብለዋል።
በዛሬው እለት ከ200 በላይ የልማት ተነሺዎች ውይይት አድርገው መግባባት ላይ መድረሳቸውም ተገልጿል።
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.