
የወንዝ ዳርቻ ልማት በመዲናችን አዲስ አበባ
"ደንቡን ተላልፈው በሚገኙ ከሁለት ሺህ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር ገንዘብ ያስቀጣል!"
አዲስ አበባ ለመመስረቷ ምክንያት ከሆኗት ወሳኝ ምክንያቶች መካከል ማራኪና ተስማሚ ውበቷ እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቷ ይጠቀሳሉ፡፡ ከእነዚህ የተፈጥሮ ጸጋዎች መካከል ደግሞ ዓመቱን ሙሉ ይፈሱ የነበሩ ንጹህ ወንዞቿ ይገኙበታል፡፡
በጊዜ ሂደት ከህዝብ ቁጥር መጨመርና ከከተሜነት መስፋፋት ጋር ተያይዞ ወደ ወንዞች በሚለቀቁ ቆሻሻዎች እንዲሁም የተለያዩ ተረፈ ምርቶችና የኢንዱስትሪ ፍሳሾች ሳቢያ ለመዝናኛ ጭምር ያገለግሉ የነበሩት የመዲናዋ ንጹህ ወንዞች በእጅጉ ተበክለው ለዕይታም ለጤናም አደገኛ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የወንዞቹ መበከል የከተማ ግብርና ላይ ለተሰማሩ አርሶአደሮችም ትልቅ ተግዳሮት መደቀኑ ይነገራል፡፡
ባለፉት 20 ዓመታት የአዲስ አበባ ህዝብ ቁጥር እንደ ሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ሁሉ ከእጥፍ በላይ እንዳደገ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ባለፉት ጊዜያት ዝናብ በዘነበ ቁጥር የመዲነዋ ወንዞች መሀል ከተማዋን በጎርፍ የሚያጥለቀልቁ ሲሆን፤ ጎርፉ ተሸክሞት የሚመጣው ቆሻሻም የነዋሪውን ጤና ለአደጋ ይዳርጋል፡፡ የመዲናዋን ንጽህናም ይበክላል፡፡
በመዲናዋ የሚገኙ ወንዞች ለበርካታ ዓመታት ትኩረትና ጥበቃ ተነፍጓቸው በመቆየታቸው ለነዋሪው ጥቅምና ውበት ከመሆን ይልቅ ጉዳትና ጠንቅ ሆነዋል፡፡ እንኳንስ የመዝናኛ ሥፍራና የቱሪዝም ማዕከል ሊሆኑ ቀርቶ፣ በይፋ የቆሻሻና ፍሳሽ መልቀቂያና ማከማቻ ተደርገው መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ይሄ ደግሞ በአፍሪካ መዲናነቷና በዓለማቀፍ ተቋማት መቀመጫነቷ ለምትታወቀው አዲስ አበባ ፈጽሞ የሚመጥናት አይደለም፡፡
በህገ መንግሥቱ አንቀፅ 44 ንኡስ አንቀፅ 1 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው፤ ሁሉም ሰው ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት ያለው ሲሆን፤ የተሻሻለው የአዲስ አበባ ቻርተር 361/1995 ህግም ይህንኑ ይደነግጋል፡፡ ምንም እንኳን ከ23 ዓመት በፊት የወጣ የብክለት መከላከል አዋጅ ህግ ቢኖርም፣ በትግበራው ላይ በነበረው ክፍተት ሳቢያ ውጤታማ ሳይሆን መቅረቱ ይታወቃል፡፡ በዚህም የተነሳ የመዲናዋ ወንዞች እጅጉን ቆሽሸውና ተበክለው አደገኛ የጤና ጠንቅ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
ከጥቂት ዓመታት በፊት ታዲያ በጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ሃሳብ ጠንሳሽነት፣ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ለማስዋብና ለማዘመን እንዲሁም ከአፍሪካ ተመራጭ መዲና ትሆን ዘንድ ያለመ የወንዝ ዳር ልማት ፕሮጀክት ተቀርጾ በይፋ መተግበር ጀምሯል፡፡
የአዲስ አበባ የወንዝ ዳር አረንጓዴ ልማት ፕሮጀክት፣ ወይም “ሸገርን የማስዋብ ፕሮጀክት” እ.ኤ.አ በየካቲት ወር 2019 ዓ.ም በይፋ የተጀመረ ሲሆን፤ ዓላማውም በዋናነት የከተማዋን ወንዞች በማጽዳት አረንጓዴና ውብ የህዝብ መዝናኛ ሥፍራ መፍጠር ነው፡፡ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ 56 ኪ.ሜ የሚረዝም ሲሆን፤ ከእንጦጦ ተነስቶ አቃቂ የፍሳሽ ማጣሪያ ጣቢያ ይደርሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቱ የመዲናዋን ወንዞች ወደ ቀድሞ ተፈጥሯዊ ማንነታቸው ለመመለስና የመዝናኛና የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ ታልሞ በትጋት እየተሰራ ይገኛል፡፡ ለአብነትም በከተማው አስተዳደር በ2ኛ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ስራዎች ከሚለሙ 8 ኮሪደሮች መካከል 21.5 ኪ.ሜ እርዝመት ያለው የእንጦጦ-ፒኮክ ወንዝ ዳርቻ ልማትና 20 ኪ.ሜ የሚረዝመው የቀበና ወንዝ ዳርቻ ልማት ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ፕሮጀክቱ በወንዝ ዳርቻዎች ላይ ስር የሰደደ ችግር ለሚታይባት አዲስ አበባ መሰረታዊ ለውጥ እንደሚያመጣም በከተማ አስተዳደሩ ጭምር ታምኖበት በቁርጠኛ አቋምና ትጋት ቀን ከሌት እየተሰራ ይገኛል፡፡
በከተማዋ እየተከናወነ የሚገኘው 2ኛው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት አንድ አካል የሆነው የወንዝ ዳርቻ ልማት፤ መዲናዋ የተፈጥሮ ፀጋዎቿን በአግባቡ ለመጠቀም በሚያስችል መልኩ ወንዞቿን ፅዱና አረንጓዴ በማድረግ፣ ለራሷም ሆነ ለተቀረው ዓለም አርአያ ለመሆን ታይቶ በማይታወቅ የለውጥ ጉዞ ላይ ትገኛለች፡፡
ይሁን እንጂ አሁንም አንዳንድ ግለሰቦችና ድርጅቶች ደረቅ ቆሻሻዎችና የኬሚካል ፍሳሾችን ወደ ወንዞች በመልቀቅ የወንዞችን ብክለት እንዲባባስ እያደረጉ ናቸው። የብክለት መጠኑ ከላይኛው ተፋሰስ ወደ ታችኛው ተፋሰስ እየጨመረ በመምጣቱ በማህበረሰቡ ላይ ከፍተኛ የጤና መታወክን እያስከተለ ይገኛል።
በዚህም ምክንያት በህገ-መንግሥቱ የተቀመጠውን መብትና ግዴታ መፈፀም የግድ ብቻ ሳይሆን ወቅቱ የሚጠይቀው አሳሳቢ ጉዳይ በመሆኑ የማህበረሰቡን ጤና የሚያውኩና የወንዞችን ብክለት የሚያባብሱና ሌሎች መሰል ተግዳሮቶችን መፍታት አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል። ወንዞችን ማልማትና ከብክለት መከላከል ካልቻልን አዲስ አበባን የማስዋብና ማዘመን ራዕያችንን እውን ማድረግ አይታሰብም፡፡
የወንዞችን ደህንነት ለመጠበቅና ከብክለት ለመከላከል በአስተዳደሩ እየተከናወነ ከሚገኙ የወንዞች ዳር ልማት ጎን ለጎን፣ አዲሱ የወንዞች ዳርቻ ብክለት መከላከል ደንብ ቁጥር 180/2017 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ፀድቆ፣ ከታህሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
ደንቡን በተገቢው ሁኔታ ተረድቶ ተግባራዊ ማድረግ ይቻል ዘንድ በተለያዩ ጊዜያት በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ የውይይት መድረኮችን በመፍጠር ከማህበረሰቡ ጋር መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን፤ አሁንም የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት በመታመኑ በወንዞች ዳርቻ አካባቢ ለሚገኙና ከጉዳዩ ጋር በቀጥታ ግንኙነት ያላቸው አምራችና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በደንቡ ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲጨብጡ እየተደረገ ነው፡፡
በከተማው የሚገኙ ወንዞች ለከተማዋ የውበት ምንጭ ሳይሆኑ የቆሻሻ መጣያ ሆነው መቆየታቸውን የሚናገሩት የአዲስ አበባ ከተማ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዲዳ ድሪባ፤ ይህ ታሪክ እንዲቀየር አስተዳደሩ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡
ከተማችን ከግብር ከፋዮች በምታገኘው ገቢ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በርካታ ፕሮጀክቶችን በማከናወን ላይ እንደምትገኝ የጠቁሙት ዋና ሥራ አስኪያጁ፤ እነዚህን የለሙና የተገነቡ ስፍራዎች ለመጠበቅ የተለያዩ ደንቦች ጸድቀው ወደ ትግበራ መገባቱን ይናገራሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ወንዞች ብክለት በአካባቢና በጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳትና መፍትሔዎች እንዲሁም የወንዞች ዳርቻ ልማትና ብክለትን ለመከላከል በወጣው ደንብ ቁጥር 180/2017 እና የቅጣት ሰንጠረዥ ዙሪያ ከማህበረሰቡ ጋር በስፋት ውይይት ተደርጎበት የጋራ መግባባትና ግንዛቤ ላይ መደረሱን አቶ ዲዳ ድሪባ አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ከግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራው ጎን ለጎን፣ ደንቡን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መወሰድ መጀመሩን ነው ዋና ሥራ አስኪያጁ የገለጹት፡፡
በአስተዳደሩ ካቢኔ በጸደቀው አዲሱ የወንዞች ዳርቻ ብክለት መከላከል ደንብ መሠረት፣ ደንቡን ተላልፈው በሚገኙ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ የገንዘብ ቅጣት የሚጣል ሲሆን፤ ዝቅተኛው የገንዘብ ቅጣት ሁለት ሺህ ብር፣ ከፍተኛው ደግሞ እስከ አንድ ሚሊዮን ብር እንደሚደርስ በሰነዱ ላይ ተመላክቷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ ማስከበር ባለስልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ ዘሪሁን ተፈራ ባስተላለፉት መልዕክት፣ንፁህ ወንዝና ጤናማ አካባቢ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት፣ ማህበረሰቡም ሆነ ተቋማት ሃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት፣ ከአስተዳደሩ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወደፊትም ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራው ተጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን፤ ደንቡን ተላልፈው በሚገኙ ግለሰቦችና ተቋማት ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ መውሰድ መጀመሩም አስታውቀዋል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.