
የህግ ማስከበርና የቁጥጥር ስራዎች ነጋዴው ተረጋግቶ ስራውን እንዲሰራ ሊያደርግ በሚያስችል ስነ ምግባር ሊመራ እንደሚገባ ተጠቆመ
የህግ ማስከበርና የቁጥጥር ስራዎች ለግብር ከፋዩ ተገቢውን ክብር በሚሰጥ፣ ነጋዴው ተረጋግቶ ስራውን እንዲሰራ ሊያደርግ በሚያስችል ስነ ምግባር ሊመራ እንደሚገባ ተጠቆመ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በ11ንዱም ክፍለ ከተማ ከሚገኙ የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ ባለሙያዎች፣ ቡድን መሪዎች እና የስራ ሂደቶች ጋር በቁጥጥር ስራዎች አተገባበር ላይ ውይይት በማካሄድ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡
በውይይቱ- የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በበጀት ዓመቱ የተጀመሩ የህግ ማስከበር ስራዎች በገቢ ላይም ሆነ የንግድ ስርዓቱ በፍትሃዊነት እንዲመራ በማስቻል ረገድ ብዙ ለውጦች የታዩበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይሁን እንጂ የቁጥጥር ስራዎችን ከብልሹ አሰራር ከማፅዳትና ከስነ ምግባር ጉድለት ጋር በተያያዘ ሰፋ ያሉ ችግሮች የሚስተዋሉ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተቋሙ እና በግብር ከፋዩ መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሻክር እንዲሁም ግብር ከፋዩ በተቋሙ ላይ ያለው እምነት እንዳይጠናከር ምክንያት ከሆኑ ጉዳዮች አንዱ በቁጥጥር ስራዎች ወቅት የሚፈፀሙ ችግሮች መሆናቸውንም አንስተዋል፡፡
ስለሆነም በአንዳንድ የቁጥጥር ባለሙያዎች ከቁጥጥር ስራዎች ጋር በተያያዘ በግብር ከፋዩ ላይ የሚደርሱ የማመናጨቅ፣ የማዋከብ እንዲሁም ክብርን የሚጎዱ ያልተገቡ አቀራረቦች እንዲስተካከሉ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ የቁጥጥር ባለሙያዎች የሚፈፅሙት የቁጥጥር ተግባር በመልካም ስነ ምግባርና ከሌብነትና ብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ መፈፀም ይገባልም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ከደረሰኝና ከመሳሰሉ ተግባራት ጋር በተያያዘ የሚደርጉ የቁጥጥር ስራዎች ህግ ከማስከበር ባለፈ ፍትሃዊነትን እያሰፈናችሁ መሆኑን መገንዘብና ህጋዊ ነጋዴው በህገወጡ ነጋዴ ከንግድ ስርዓቱ እንዳይወጣ ለማድረግ የሚከናወን መሆኑን በአግባቡ መረዳት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በመሆኑም የቁጥጥር ስራዎች ዋነኛ አላማው ህጋዊ ነጋዴው ተረጋግቶ የንግድ ስራውን እንዲያከናውን የሚያደርግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ በከተማ አስተዳደሩ የንግድ ስርዓቱ በፍትሃዊነት እንዲመራና ለሁሉም ነጋዴ እኩል የመወዳደሪያ ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የሚያስችል መሆን እንደሚገባው ከግንዛቤ ማስገባት ወሳኝ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
ስለሆነም የቁጥጥር ባለሙያዎች በመልካም ስነ ምግባር ለግብር ከፋዮች ተገቢውን ክብር በመስጠትና ከብልሹና ከሌብነት ድርጊት በመፅዳት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማሳሰባቸውን ከገቢዎች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.