.png)
ኮንሶዎች በኮሪደር ልማቱ አሻራቸውን እያስቀመጡ ነው::
የኮንሶ ባህላዊ የእርከን ሥራ - ከኮንሶ እስከ አዲስ አበባ
የተፈጥሮ ሃብት ልማትን ለመጠበቅ ፈታኝ የሆነውን መልከዓ ምድር በእርከን ስራ ለእርሻ ያዋሉትና ተፈጥሮን ተንከባክበው በትውልድ ቅብብሎሽ ያቆዩት የድንቅ ባህል ባለፀጋዎች ናቸው፤ የኮንሶ ማህበረሰቦች፡፡
ህይወታቸው በእጅጉ ከተፈጥሮ ጋር የተቆራኘው የኮንሶ ማህበረሰቦች፤ ተፈጥሮን በመጠበቅና በመንከባከብ ይታወቃሉ፡፡ ኮንሶዎች ከተፈጥሮ ጋር ባደረጉት የረጅም አመታት ትግል የአካባቢውን መልክዓ-ምድር በባህላዊ የእርከን ሥራ በፈለጉት መንገድ ለመቀየርና ለመጠቀም የቻሉ ሲሆን፤ በዚህም ከሀገራቸው አልፈው ዓለምን በማስደመም የራሳቸውን ታሪክ ሠርተዋል።
ኤ.አ.አ. በ2011 ዓ.ም በዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የኮንሶ ማራኪ መልክዓ-ምድር፤ 23 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ነው፡፡ መልክዓ- ምድሩ፣ በውስጡ በተለያዩ ባህላዊ ዘዴዎች የተሰሩ እርከኖችና ካቦች የታጠሩ መንደሮች እንዲሁም ጥብቅ ደኖችን ጭምር ያካተተ ነው፡፡ የኮንሶ የድንጋይ እርከኖች በዓይነታቸውም ሆነ በአሰራራቸው ውበትን የሚያጎናፅፉና የአካባቢውን መልከዓ-ምድር የሚጠብቁ ናቸው፡፡
ለኮንሶዎች ብቻ ሳይሆን እንደ ሀገር ኩራት የሆነው ባህላዊ የእርከን አሰራር በኮንሶ ብቻ ሳይገደብ፣ 24 ሰዓት ሳታንቀላፋ ለእድገት በምትታትረው የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባም እየተተገበረም ይገኛል፡፡ ኮንሶዎች የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ባደረገባቸው የእንጦጦና ሌሎች የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች ላይ የእርከን ሥራ ጥበባቸውን መተግበር ከጀመሩ ሰነባብተዋል፡፡ በዚህ ሥራቸውም በመዲናዋ ላይ አሻራቸውን እያሳረፉ ይገኛሉ።
በኮሪደር ልማቱ የአፈር መሸርሸር እንዳይከሰት የእርከን ስራዎችን ሲያከናውኑ ያገኘናቸው ከኮንሶ ማህበረሰብ የመጡት የእርከን ሥራ ባለሙያ አቶ አማኑዔል አክመል፣ተወልደው ያደጉት በደቡብ ኢትዮጵያ ኮንሶ ዞን ከአራት ከተማ ሲሆን፤ በደንና መሬት ጥበቃ ሥራ ላይ መሰማራታቸውን ይናገራሉ፡፡
"እኔ ከመጣሁ ጀምሮ እስከ አሁን እየሰራን ያለነው በወንዞች ዳርቻ ሲሆን፤ የኮሪደር ልማት ስራዎቹ በጣም በጥሩ ሁኔታ እየተካሄዱ መሆናቸውን አይተናል። የኮንሶ ልጆችም እርከኑን በመስራት አሻራቸውን እያስቀመጡ ናቸው፡፡ በእኔ በኩልም ቱሪስቶች ሊጎበኙት የሚችል፣ውብና ጥራት ያለው ስራ ሰርተን ከተማችን ላይ አሻራችንን ማስቀመጥ እንፈልጋለን፡፡ አሁንም ከመንግሥት ጋር በኮሪደር ልማት ዙሪያ ጠንካራ ሥራዎችን እየሰራን እንገኛለን፡፡" ብለዋል፤ አቶ አማኑዔል፡፡
በኮሪደር ልማቱ ስለተፈጠረላቸው የሥራ እድልም ሲናገሩ፤ "ለበርካታ ኮንሶ ወጣቶች የስራ እድል ከመፈጠሩ ባሻገር ከምናገኘው ገቢ በመቆጠብ ቤተሰቦቻችንን ለመርዳት እንዲሁም ወደፊት ለመነገድም ሆነ በተለያየ ሙያ ለመሰማራትና ኑሮአችንን ለማሻሻል የምንችልበት አጋጣሚ ተፈጥሮልናል፡፡" ይላሉ፡፡
የኮንሶ የእርከን አሰራር ከቅድመ አያቶቻችን ሲወርድ ሲወራረድ የመጣ ነው የሚሉት አቶ አማኑዔል፤ ይህ ጥንታዊ የሆነ የእርከን ሥራ ኮንሶን በዩኔስኮ እንድትመዘገብ ያደረገ ጥበብ መሆኑን ያወሳሉ፡፡ እኛም አባቶቻችን ያስረከቡንን ጥበብ ይዘን በዚህ የልማት ስራ ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን ለልጆቻችንም ጭምር አሻራችንን እያኖርን ነው፤ብለዋል፡፡
"በተለያየ ምክንያት ወደ መዲናዋ የሚመጡ የኮንሶ ልጆች በእኛ እጅ የተሰሩ ስራዎችን ሲያዩ፣ እነሱም የራሳቸውን ታሪክና አሻራ ለማኖር መነቃቃት ይፈጥርላቸዋል።" ሲሉም አክለዋል፡፡
የእርከን ስራዎች ዋና ዓላማ መሬት በጎርፍ እንዳይሸረሸር መከላከልና አካባቢን ማስዋብ መሆኑን የገለጹት አቶ አማኑኤል፤ እኛም በአካባቢያችን ለእርሻ አስቸጋሪ የሆኑ ቦታዎችን በማስተካከልና እርከን በመስራት ነው የምንጠቀመው፤ ብለዋል፡፡ ከልምድና ተሞክሮአችን ተነስተን ከኮንሶ በተሻለ ሥራውን በማስፋትና በማጠናከር እንሰራለን ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የእርከን ሥራ በህብረትና በአንድነት መሥራትን ይፈልጋል ይላሉ፤ አቶ አማኑኤል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዱ፤ "የእርከን ሥራ የተለያዩ አሰራሮችን በየደረጃው የሚፈልግ ነው፡፡ አንዱ መሰረት ሲጥል ሌላው ድንጋይ ይጠርባል፤ የተጠረበውን ድንጋይ ሌላው ሲደረድር አፈር የሚሞላም አለ፤ ስራው የሰው ኃይል ስለሚፈልግ እነዚህን ተግባራት በሙሉ አቅም ለመፈፀም በህብረት መስራት ያስፈልጋል፡፡" ብለዋል፡፡
"በህብረት በመስራታችን ደግሞ ህብረ-ብሄራዊነትን፣ አንድነትንና ኢትዮጵያዊነትን እያሳየን ነው፡፡ ይህ ለወደፊቱ የብልፅግና ጉዞ መሰረት ነው ብዬ አስባለሁ፡፡" ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ሌላው የእርከን ሥራ ባለሙያ ደግሞ አቶ ያቤና ያኬሳ ይባላሉ፡፡ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከኮንሶ ዞን ከነአ ወረዳ ነው የመጡት፡፡ እዚህ አዲስ አበባ የመጡት ከአዲስ አበባ ከንቲባ ፅ/ቤት በተደረገላቸው ጥሪ፣ በከተማዋ የወንዝ ዳርቻ ልማት ላይ ለመሳተፍ መሆኑን ይናገራሉ፡፡
በከተማዋ እየተከናወነ ያለውን የወንዝ ዳርቻ ልማት በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፤ "እጅግ በጣም የሚያኮራ የልማት ሥራ እየተሰራ እንደሚገኝ ለማየት ችለናል፡፡ እኛም በልማቱ እየተሳተፍን በመሆናችን በጣም ደስተኞች ነን፡፡" ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተፈጠረላቸውን የሥራ እድል አስመልክቶ ሲናገሩም፤ ለኮንሶ ልጆች ትልቅ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ጠቁመው፣ እዚህ በቀን የሚያገኙት ዕለታዊ ገቢ በኮንሶ ከሚያገኙት ጋር ጨርሶ የሚነጻጸር እንዳልሆነ ይናገራሉ፡፡
"እኛ ጥቅምት ላይ በመጀመሪያ ዙር የመጣን ነን፤ስድስተኛ ወራችንን ይዘናል፡፡ በኮንሶ እለታዊ ገቢያችን ዝቅተኛ ነበር፡፡ እዚህ ምግብና ልብስን ሳይጨምር በቀን 650 ብር እናገኛለን፤ በወር ከ19 ሺ ብር በላይ ይደርሰናል፡፡ ይህ ደግሞ ለአንድ አርሶ አደር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡" ብለዋል፡፡
በዚህ ገቢም የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ እየቀየሩበት፣ ልጆቻቸውን እያስተማሩበትና የተቸገሩ ዘመዶቻቸውን እየረዱበት መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ ሥራው በጣም አድካሚ ቢሆንም፣ የዚያኑ ያህል ተጠቃሚ መሆናቸውን አልሸሸጉም፡፡
መጀመሪያ ላይ በዚህ ሥራ ላይ ከኮንሶ የመጡ 50 ባለሙያዎች ብቻ ተሰማርተው እንደነበር ያስታወሱት አቶ ያቤና፤ አሁን ላይ ከ400 ያላነሱ ባለሙያዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡
የኮንሶ ባህላዊ የእርከን ሥራ ታሪካዊ ዳራን በተመለከተ ሲያብራሩም፤ "የኮንሶ ማህበረሰብ በተፈጥሮው ታታሪ ህዝብ ነው፡፡ መልክዓ ምድሩም ሲታይ አብዛኛው ተራራማ፣ አሸዋማና ዝናብ አጠር ነው፡፡ ይሄ አካባቢ ታዲያ በምን አይነት ዘዴ ነው ለረጅም አመታት የኖረው ቢባል በአፈርና ውሃ ጥበቃ ዘዴ ነው፡፡ ይህም ከጥንት ጀምሮ አፈር በጎርፍ ተጠርጎ እንዳይሄድ ሲሰራበት የኖረና እንደ ባህል የተወሰደ ልምድ በመሆኑ ከትውልድ ትውልድ እየተሸጋገረ እኛ ዘንድ ደርሷል፡፡ እኛም እዚህ ተገኝተን ልምዳችንንና አሻራችንን እያኖርን ነው፡፡" ብለዋል፡፡
ከደቡብ ኢትዮጵያ ኮንሶ ዞን የመጡት አቶ ከድረው ገበየሁ እንዲሁ በመዲናዋ እየተከናወነ በሚገኘው የወንዝ ዳርቻ ልማት ላይ የተለያዩ የእርከን ካብ ስራዎችን እየሰሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ፡፡ ከእንጦጦ ተራራ ወደ ከተማው የሚፈሰው ወንዝ አፈሩን እንዳይሸረሽር፣ የጎርፍ መጥለቅለቅ እንዳይከሰትና የተክሎቹ ስር እንዳይነቃቀል እንዲሁም የወንዝ ዳርቻዎችን ውበት ለማስጠበቅ የእርከን ስራ እየተሰራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
ሥራውን የለመድነው ከአያቶቻችን በማየት ነው የሚሉት አቶ ከድረው፤ የአዲስ አበባ ወጣቶችም ከእኛ ልምድ ቢቀስሙና ከተማቸውን ቢያለሙ ተጠቃሚ ይሆናሉ ባይ ናቸው፡፡
"እኛ በአሁኑ ወቅት እየሰራን በምናገኘው ገንዘብ ህይወታችንን እየቀየርን ነው፤በዚህም በጣም ደስተኞች ነን፤ሥራችን አልቆ ጥርት ያለ ውሃ በወንዝ ሲፈስ ስናይ ደግሞ ከዚህ የበለጠ ደስተኞች እንሆናለን፡፡" ሲሉም ስሜታቸውን ገልጸዋል፡፡
ከኮንሶ ምድር መጥተው በኮሪደር ልማቱ ላይ እየተሳተፉ ያሉና ያነጋገርናቸው ባለሙያዎች በሙሉ ይህንን መልካም የሥራ ዕድል ለፈጠሩላቸው የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤና ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ልባዊ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ይሄ ከኮንሶ ምድር አልፎ በመዲናዋ የኮሪደር ልማት ላይ እየተተገበረ የሚገኝ የኮንሶ ባህላዊ የእርከን ሥራ በክልሎችም ቢዳረስ ጠቀሜታው የትየለሌ ነው ብለን እናምናለን፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.