በለውጡ 7 ዓመታት ብዙ ተግዳሮቶች የታለፉበት እ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በለውጡ 7 ዓመታት ብዙ ተግዳሮቶች የታለፉበት እና በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው!! :- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

በለውጡ 7 ዓመታት ብዙ ተግዳሮቶች የታለፉበት እና በርካታ ስኬቶች የተመዘገቡበት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡

በተለይም የፖለቲካ ባህል ላይ ያለውን ስብራት በመጠገን የፖለቲካ ባህል እየተለወጠ የመጣበት፣ ሀገራዊ ስብራቶች መጠገን የጀመሩበት፣ የኢኮኖሚ ስብራቶችም ከመሠረቱ መታከም የጀመሩበት፣  መሠረት የተጣለበት እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡

በዚህ ረገድ አዲስ አበባ ትልቅ የለውጡ ማሳያ መሆኗን ያነሱት ከንቲባዋ፣ ለውጡን ማየት እና ማገናዘብ ለፈለገ አዲስ አበባ ዋና ማሳያ ናት ሲሉ ገልጸዋል፡፡

በመዲናዋ የኢትዮጵያን ብልጽግና ለማሳካት የሚያስችሉ መሠረቶች መጣላቸውንም ነው ያመላከቱት፡፡

ለዚህም ዋነኛው ማሳያ የሥራ ባህላችን መቀየሩ ነው ያሉት ከንቲባ አዳነች፣ የሥራ ሰዓት ተጠብቆ እና እረፍት ተደርጎ ብልፅግናን ማረጋገጥ የማይቻል በመሆኑ ሌት ተቀን የመስራት አስፈላጊነት ላይ ታምኖበት ወደ ተግባር መገባቱ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በድህነት የተጎዳች ሀገር እንደመሆኗ ኢትዮጵያውያን ክብራቸው የሚነካበት እና የሀገር ክብር የሚዋረድበት ሁኔታ የነበረበትን በማስታወስም፣ ከዚህ ዝቅታ ለመውጣት ለከተማዋ ነዋሪዎችና ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ለመስራት የተደረገው ጥሪ በጎ ምላሽ በማግኘቱ አዲስ አበባ ላይ የሀገርን መፃኢ ዕድል የሚያሳዩ መሠረታዊ ሥራዎች መሰራት መቻላቸውን ገልጸዋል፡፡  

እጦት የአስተሳሰብ እንጂ በኢትዮጵያ መሬት ላይ እሴት ተጨምሮበት ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ሀገርን የሚያበለፅግ እጦት ኖሮ አለመሆኑንም አመላክተዋል፡፡

ከምጣኔ ሀብት አኳያም አዲስ አበባ ከሀገሪቱ አጠቃላይ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ 40 ከመቶ ድርሻ እንዳላት የጠቀሱት ከንቲባ አዳነች፣ ይህም ከለውጡ በፊት ከነበረው ከ8 እጥፍ በላይ እድገት ማሳየቱን ነው የገለጹት፡፡

2010 ዓ.ም ላይ የከተማዋ ዓመታዊ ገቢ ከነበረበት 30 ቢሊየን ብር በ2017 በጀት ዓመት እስከ መጋቢት ወር ወደ 150 ቢሊየን ብር ገቢ እንደተሰበሰበ እና በዓመቱ መጨረሻ 230 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

ይህም ሊሆን የቻለው በህዝቡላይ ግብር በመጨመር ሳይሆን ግብር የማይከፍሉ ወደ ግብር ሥርዓቱ እንዲገቡ በማድረግ የግብር ፍትሀዊነትን በማረጋገጥ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በለውጡ ዓመታት በርካታ ፕሮጀክቶች መገንባታቸውን በማንሳትም ፕሮጀክቶቹ የመዲናዋን የኢኮኖሚ ዕድገት ከመጨመር ባለፈ ለነዋሪዎች የኑሮ ጫናን የሚያቀሉ ስለመሆናቸው ተናግረዋል፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.