.png)
ወቅቱ በሚጠይቀዉ ልክ ምልአተ ሕዝቡን ለመድረስ የኮሙኒኬሽን ሥራችንን ዓላማ ተኮር ማድረግ ይገባል፡- ዶ/ር ለገሠ ቱሉ
የበይነ መረብ ዓውዱ እና ውስብስብ ፍላጎቶች የፈጠሩትን የድኅረ እውነት ወቅት ፈተና ለመቋቋም የሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ሥራዉን ከተለመደዉ መንገድ በማውጣት ወደ ዓላማ ተኮር ማሸጋገር እንደሚገባ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሠ ቱሉ አስገነዘቡ፡፡
“ዓላማ ተኮር ተግባቦት ለኢትዮጵያ መንሰራራት” በሚል መሪ ሐሳብ ለክልል እና ከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ በሚገኘዉ የዐቅም ግንባታ ሥልጠና ላይ ነው ሚኒስትሩ ይህንን ያስገነዘቡት፡፡
የበይነ መረብ ዓውዱ የመረጃ ፍሰቱን ከአንድ ወደ ባለብዙ አቅጣጫ የቀየረ እና የመረጃ ስርጭት ፍጥነቱንም በእጅጉ ያሳደገ በመኾኑ ይህንን ኹኔታ ያገናዘበ የመንግሥታዊ መረጃ ስርጭት መኖር እንደሚገባዉ አመላክተዋል፡፡ “ወቅቱ በሚጠይቀዉ ልክ ምልአተ ሕዝቡን ለመድረስ የኮሙኒኬሽን ሥራችን ዓላማ ተኮር ማድረግ፤ በስትራቴጂ መምራት እና ኹሉንም የተግባቦት አማራጮች በመጠቀም የሕዝቡን የመረጃ ፍላጎት ማሟላት ልናተኩርባቸዉ የሚገቡ ናቸው” ብለዋል፡፡
የአገልግሎቱ ሚኒስትር ድኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ ደግሞ የኮሙኒኬሽን ዘርፉ ከሚዲያ ጋር ያለዉን ግንኙነት በመግራት በአጀንዳ የመምራት ኀላፊነቱን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡ “በኮሙኒኬሽን መዋቅሩ እና ሚዲያ መካከል ጤናማ፣ በዕቅድ የሚመራ እና የኢትዮጵያን መሻት የሚያሳካ መስተጋብር መኖር አለበት፡፡ በሁለቱ ዘርፎች መካከል ያለው ግንኙነት መጠናከር የመንግሥት እና ሕዝብ ፍላጎቶችን ለማገናኘት፤ ዘላቂ ብሔራዊ ጥቅሞችን እና መዳረሻ ትልሞችን ለማስረጽ ያስችላል” ብለዋል፡፡
የኮሙኒኬሽን ዘርፉ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ሚዲያዉን በአጀንዳ በመምራት የሐሰተኛ መረጃ ስርጭትን እና የመረጃ ብክለትን በመቀነስ የመንግሥትን አኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኹለንተናዊ አቅጣጫዎች በመልእክቶች አማካኝነት እንዲያስገነዘብ በውጤቱም ምልአከተ ሕዝቡን እንዲያሳትፍ አቶ ከበደ አሳስበዋል፡፡
በአፍሪካ የአመራር ልሕቀት አካዳሚ ከመጋቢት 29/2017 ዓ.ም ጀምሮ እየተሰጠ ባለዉ የዐቅም ግንባታ ሥልጠና ከ220 በላይ የክልል እና የከተማ አስተዳደር የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አመራሮች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው፡፡ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዘርፉን በመረጃ ሥርጭት እና አጀንዳ ከማቀናጀት እና ማናበብ በተጨማሪ በዐቅም ግንባታ ሥራዎች ወደላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተደጋጋሚ ሥልጠናዎችን እየሰጠ ይገኛል፡፡
ለተጨማሪ የመረጃ አማራጮች
https://linktr.ee/addisababacommunication
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.