በትላንትናው እለት ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኝ የተ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

በትላንትናው እለት ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኝ የተባረክ መስጂድ አጥር ፈረሰ በሚል በአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ለወጣው መግለጫና በተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘዋወር ለነበረው መረጃ ከቂርቆስ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የተሰጠ መግለጫ

በቀን 05/08/2017 ማለትም በዛሬው እለት እሁድ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ልዩ ቦታው ሜክሲኮ አካባቢ የመንግስት አካላት የመስጂድ አጥርን አፈረሱ የሚል መረጃ የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤትን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘዋወር መዋሉ ይታወቃል።

እንደሚታወቀው የክፍለ. ከተማው አስተዳደር ማንኛውም የመንግስትና የህዝብ ጥቅምን የሚጎዱ ህገወጥ ድርጊቶች ሲፈፀሙ በህግ አግባብና ህጋዊ ውሳኔን መነሻ በማድረግ እየተከላከለ ቆይቷል። ወደፊትም የሚተገብረው ትልቁ ኃላፊነቱ ነው።

በዛሬው እለትም በተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘዋወር የዋለው መረጃ መንግስት ዉሳኔ ያልሰጠበት መሬትን ያለአግባብ ከህግ ዉጪ ለመያዝ የተደረገ ተግባራዊ እንቅስቃሴን ለመከላከልና የህግ የበላይነት ለማረጋገጥ የተወሰደ እርምጃ ሲሆን ጉዳዩን በተሳሳተ መንገድ መተርጎም በምንም ዓይነት ተቀባይነት ያለው ድርጊት አይሆንም። ህዝባችንም እጅግ አስተዋይ ህዝብ በመሆኑ ጉዳዩን በሚዛኑ የሚረዳ እንደሚሆን እናምናለን።

በክ/ከተማችን የሚገኘዉ ተባረክ መስጂድ የክፍለ ከተማው አስተዳደር ከመስጂዱ አባቶችና ምዕመናኑ ጋር በቅርበት አብሮ ከሚሰራቸው፣ ወደፊትም አብሮነቱን ከሚያጠናክራቸው የእምነት ተቋማት መካከል አንዱ ነው።

ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ የመስጂዱ አስተዳደር ከህጋዊ ይዞታዉ ዉጪ ያለ መሬት ላይ የማስፋፊያ ጥያቄ ለአስተዳደሩ አቅርቧል በሚል ሰበብ ለሀገራዊ ፕሮጀክት ሲባል በቦታዉ የነበሩ ነዋሪዎችና የፌደራል ፖሊስ ካምፕን ወደ ሌላ ቦታ በማዛወር የፀዳ ቦታን የመስጂድ ይዞታ እንደነበረ አስመስሎ ማቅረብ ተገቢ የሆነ መረጃ አይደለም።

ቦታው ከዚህ በፊት የፌደራል ፖሊስ ካምፕና የነዋሪዎች የነበረ ሲሆን ቦታውን በማፅዳት ሀገራዊ ፋይዳ ላለዉ ፕሮጀክት በሀገራዊ ፕሮጀክት ኮንትራክተሩ አማካኝነት ሙሉ ባዶ ቦታዉ በኤጋ ቆርቆሮ እንዲታጠር ተደርጎ የቆየ ነው።

ነገር ግን ይህ እውነት ሆኖ ሳለ አሁን ግን ቦታውን ያለምንም ህጋዊ ፍቃድ የመስጂዱ እንደሆነ በማስመሰል በመንግስት የታጠረዉን ቦታ ያለምንም ህጋዊ ፍቃድ የመስጂዱን ታፔላ እና በር በመስራት የመስጂዱ አካል በማስመስል ህገ ወጥ ተግባር ከመፈጸሙም በተጨማሪ በመስጂዱ ይዞታ ስር ያልነበረ ቦታ መንግስት አፈረሰዉ በሚል እየተሰጡ ያሉ መግለጫዎች ፍፁም ህጋዊ መሰረት የሌላቸዉ መሆኑን የእምነቱ አባቶችና ተከታዮች በሚገባ ልትረዱት ይገባል።

ያለአግባብ በተዛባ መረጃ ላይ ተመስርታችሁ ያልተገባ እንቅስቃሴ የምታደርጉ አካላትም ከድርጊታችሁ መታቀብና ቀረብ ብሎ መረጃና ማስረጃ አጣርቶ መረዳትን እንድታስቀድሙ አበክረን እያሳሰብን ክፍለ ከተማው ተጨማሪ መረጃ ለሚፈልግ ለማንኛውም አካል መረጃ ለመስጠት በሩ ክፍት መሆኑን ለማሳወቅ ይወዳል።


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.