
በአዲስ አበባ ግንባር ቀደም የሆነ የትምህርት፣ የምርምር፣ የፈጠራ እና የባህል የዩኒቨርሲቲ መንደር ልማት ትግበራ በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ፕላን እና ልማት ቢሮ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
ትግበራው የአካባቢ ልማትና የከተማ ዲዛይን ተዘጋጅቶ ደረጃ በደረጃ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አቅፎ የሚለማ መሆኑን የገለጹት የፕላን ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ ናቸው፡፡
ቢሮዉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በ4ኛ ዓመት 9ኛ መደበኛ ስብሰባው ላይ ከአራት ኪሎ እስከ ሽሮ ሜዳ ያለዉ አካባቢ የዩኒቨርሲቲ መንደር እንዲሆን ያፀደቀዉን የውሳኔ ሀሳብ መነሻ በማድረግ በአተገባበሩ ዙሪያ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የፕላንና ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑሪ በጋዜጣዊ መግለጫቸዉ እንደገለፁት የ ዩኒቨርሲቲ መንደሩ የ10 ዓመት ዕቅድ የያዘ ዝርዝር የአካባቢ ልማትና የከተማ ዲዛይን ተዘጋጅቶለት ደረጃ በደረጃ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል አቅፎ የሚለማ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አቶ አደም አያይዘውም የ4 ኪሎ፣ 5 ኪሎና 6 ኪሎ አካባቢ የዩኒቨርሲቲ እና ሌሎች የትምህርት አገልግሎት መስጫ ተቋማት የሚገኙበት ቢሆንም በአብዛኛው የታጠሩና ለማህበረሰቡ ክፍት ሆነው የሚጠበቀውን የጋራ ጥቅም ማስገኘት ያልቻሉ ናቸው፡፡
በመሆኑም በከተማዋ መዋቅራዊ ፕላን የመሬት አጠቃቀም ምድብ አንጻር የቦታ አጠቃቀም ክፍተቶች መኖራቸዉ እንደምክንያት ጭምር በመውሰድ የዩኒቨርሲቲ መንደሩም 500 ሄክታር የሸፈነ ጥናት መደረጉን ገልፀዉ ፤ የዩኒቨርስቲ መንደር ኮሪደሮችን ከማስተሳሰር በተጨማሪ በአፍሪካየዲፕሎማሲያዊ ዋና ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ በ2027 ዓ.ም ግንባር ቀደም የሆነ የትምህርት፣ የምርምር፣ የፈጠራ እና የባህል መንደር ለማልማት እንዲያስችል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ማፅደቁን ጠቁመዋል፡፡
በሌላ በኩል በዩኒቨርሲቲ መንደሩ መገንባት ዘላቂና ህይወት ያለው ደህንነቱ የተረጋገጠ የከተማ ማዕከል እንዲኖር፤የተሻለ ማህበራዊ ግንኙነት ለመፍጠር፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂ ለሆኑ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ማዕከልነት ብቁ ሆኖ እንዲገኝ፣ተወዳዳሪ የፈጠራ ማዕከል ለማበርከት እና በምርምር፣በቴክኖሎጂ እንዲሁም በንግድ ኢንኩቤሽን አማካኝነት ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታሳቢ ያደረገ መሆኑን በማብራሪያቸዉ ገልፀዋል፡፡
በተያያዘም በመግለጫው በተባባሪነት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተሳተፉት ኢሳያስ ገብረዮሐንስ (ዶ/ር) በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎችና የትምህርት ተቋማት አጥራቸውን ከፍተው ለነዋሪዎች አገልግሎት የሚሰጡበት፣ የአፍሪካ ሃገራት የፈጠራ ስራዎች የሚከናወኑበት፣ ቤተዕምነቶች የሚጠበቁበት፣ ጭስ አልባ ኢንዱስትሪዎች የሚለሙበት ጥናት መሆኑን በመግለጫው ተናግረዋል፡፡
ቢሮዉ በከተማዋ ውስጥ የሚገኙ የምርምር ማዕከላት ወደዚህ መንደር እንዲገቡ ማድረግ፤ ከእንጦጦ እስከ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ድረስ ቀጣይነት ያለው የከተማ ልማትና አረንጓዴ መሰረተ ልማት መፍጠር ከዩኒቨርሲቲ መንደሩ የሚጠበቁ ተጨማሪ ውጤቶች መሆናቸውን ተናግረዋል፡:
በኮሪደርና በሌሎች የልማት መስኮች ያሳየነውን የይቻላል አቅም ጥናቱን ወደ ተግባር በመለወጥ ረገድ ላይም ሁላችንም ተቀናጅተን በመስራት የራዕዩን ፍሬ ለትውልድ ለማኖር ህብረተሰቡ የበኩሉን በጎ አስተዋፅዖ እንዲያደርግ ጥሪያቸውን አስተላልፏል፡፡
Comments
ምንም አልተገኘም.
አስተያየቶችዎን ይተዉት.