ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎችና ተርሚናሎች ለተሳለጠ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎችና ተርሚናሎች ለተሳለጠ የትራንስፖርት ፍሰት

ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከእለት እለት በፍጥነት እያደገ የመጣው የተሽከርካሪዎች ቁጥር የትራፊክ መጨናነቅን በመፍጠር ለዘርፈ ብዙ ችግሮች እየዳረገ ነው፡፡ እኒህን ችግሮች ለመቅረፍ በመፍትሄነት ከሚጠቀሱት መካከል ደህንነታቸው የተጠበቀ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች ይገኙበታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በቴክኖሎጂ የታገዙ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች የዘመናዊ ከተሞች መገለጫ ሆነዋል፡፡  

ከሌሎች ሀገራት አንፃር በሀገራችን ያለው የተሽከርካሪዎች ቁጥር  ከፍተኛ  የሚባል ባይሆንም፣ በመዲናችን  በትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ  ያሰቡበት ሥፍራ  ባሰቡበት ሰዓት  መድረስ አዳጋች እየሆነ መጥቷል፡፡ ሰራተኞች የስራ ቦታቸው የሚደርሱት ዘግይተው ነው፡፡ ተማሪዎች ት/ቤት አርፍደው  ይደርሳሉ፡፡ ይሄ ደግሞ ጊዜን በማባከን ምርታማነትና ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡  ከዚህም ባሻገር የትራፊክ መጨናነቅ ከመኪና አደጋ መንስኤዎች አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ለበርካታ ዘመናት በመዲናዋ  ዋና የአስፓልት መንገዶች ላይ በግራና ቀኝ ማንኛውንም ተሽከርካሪ ማቆም  መብት ሆኖ ቆይቷል፡፡ እነዚህ ከሥርዓት ውጭ በዋና መንገዶች ላይ  የሚቆሙ ተሽከርካሪዎች ደግሞ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ በመፍጠር የትራንስፖርት ፍሰቱን ያስተጓጉሉታል፡፡ ለመንገድ ደህንነት ስጋትና አደጋም ያጋልጣሉ፡፡

በግልጽ እንደሚታወቀው መዲናችን አዲስ አበባ ከዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎች ጋር የተያያዘ የቀደመ ታሪክና ልምምድ ብዙም የላትም፡፡ ከሀገራዊ ለውጡ ማግስት ጀምሮ ግን  አዳዲስና በቴክኖሎጂ የታገዙ ዘመናዊ  የመኪና ማቆሚያ ስፍራዎችን በተለያዩ አካባቢዎች መገንባት የተቻለ ሲሆን፤ ይህም በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ ከመቀነስ ባሻገር ለመዲናዋም ዘመናዊ ገጽታን እያላበሳት ይገኛል፡፡  

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ችግሩን ከምንጩ ለመፍታት በማለም የረጅምና የአጭር ጊዜ እቅድ አውጥቶ እየሰራ ሲሆን፤ በሁሉም አካባቢዎች በኮሪደር ልማቱ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎችንና ተርሚናሎችን እንዲሁም  የሳይክልና የእግረኛ መንገዶችን በስፋት በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

ዘመናዊ የመኪና ማቆምያ ሥፍራዎች ከሚሰጡት ጠቀሜታዎች መካከል የሚከተሉት ይገኙባቸዋል፡-

የትራፊክ መጨናነቅን ይቀንሳሉ፤

የትራንስፖርት ፍሰትን ያሳልጣሉ፤

የመንገድ ደህንነትን ለማረጋገጥ ያግዛሉ፤

የትራፊክ አደጋን ይቀርፋሉ፤

የመኪና  ስርቆትን ይከላከላሉ፤

የጊዜና የነዳጅ ብክነትን ያስቀራሉ፤

የኢኮኖሚና ቢዝነስ እንቅስቃሴን ያቀላጥፋሉ፤

  ምርታማነትን ያሳድጋሉ፤

በቅርብ ዓመታት ውስጥ በመዲናዋ ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩት ዘመናዊ  የመኪና ማቆምያ ሥፍራዎች መካከል ከመሬት በታች (አንደርግራውንድ) የተገነባው  የመስቀል አደባባይ  የመኪና ማቆሚያ ስፍራ ተጠቃሽ ሲሆን፤ በአንድ ጊዜ  ከ1ሺህ 400 መቶ በላይ መኪኖችን የማስተናገድ አቅም አለው፡፡ መስቀል አደባባይ በየዓመቱ በርካታ የተለያዩ  ህዝባዊ ኹነቶችን የሚያስተናግድ አደባባይ ከመሆኑ አንጻር፣ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራው ያለው ፋይዳ  ከፍተኛ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

አንድነት  የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ፣ ሌላው ተጠቃሽ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ ሲሆን፤ አውቶቡሶችን ጨምሮ በአንድ ጊዜ ከ1ሺህ በላይ መኪኖችን  የማስተናገድ አቅም ያለው ነው፡፡ ይህ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ የተሽከርካሪዎችን እንቅስቃሴ  ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ከ200 በላይ ካሜራዎችን ጨምሮ የተለያዩ ቴክኖሎጂዎች የተገጠሙለት ነው፡፡ በ1.2 ሄክታር ቦታ ላይ የተገነባው አንድነት የመኪና ማቆሚያ ህንጻ፣ በውስጡ የባንክ፣ የሬስቶራንትና ሌሎች የቢዝነስ አገልግሎቶችንም ይሰጣል፡፡

በተመሳሳይ የአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየምም  በአንድ ጊዜ  ከ1ሺህ በላይ ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ የሚችል ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራ ያለው ሲሆን፤ ሙዚየሙን ለሚጎበኙም  ሆነ ለፒያሳና አካባቢዋ ምቹና ቀልጣፋ  የፓርኪንግ አገልግሎት በመስጠት የትራፊክ መጨናነቅን  እየፈታ ይገኛል፡፡

በተለምዶ ሾላ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ደግሞ  ራሱን ችሎ ለመኪና ማቆሚያነት የሚያገለግል (የካ 2)  ፕሮጀክት በፍጥነት እየተከናወነ  ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ በአንድ ጊዜ ከ1ሺህ ያላነሱ ተሽከርካሪዎችን  የማስተናገድ አቅም ይኖረዋል፡፡ ይህም በአካባቢው የሚስተዋለውን የመኪና መጨናነቅና ግርግር በማስቀረት የትራፊክ ፍሰቱን ፈጣንና ቀልጣፋ እንደሚያደርገው ይታመናል፡፡

እንግዲህ እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸው  ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች በአጠቃላይ ከ4ሺ 400 በላይ ተሽከርካሪዎችን  ማስተናገድ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ የከተማዋ ማስተርፕላን እ.ኤ.አ በ2027 በመዲናዋ የትራፊክ መጨናነቅን ለመቀነስ 60 የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎች መገንባትን ያካትታል፡፡

ይህን ለማሳካትም የከተማ አስተዳደሩ በሁሉም አካባቢዎች ተጨማሪ አዳዲስ የመኪና ማቆሚያዎችንና ተርሚናሎችን እየገነባ ሲሆን፤ አብዛኞቹም  በመጠናቀቅ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ፡፡ ለአብነትም የሚከተሉት ይጠቀሳሉ፡-

አራት ኪሎ የባስና ታክሲ ተርሚናል፣ ፓርኪንግ (G-2) እና ፕላዛ ግንባታ (86 በመቶ)፣

ፒያሳ የባስና ታክሲ ተርሚናል፣ ፓርኪንግ (G- 2) እና ፕላዛ ግንባታ (56 በመቶ)፣

ደጎል አደባባይ የታክሲ ተርሚናል፣ፓርኪንግ (G-2) እና ፕላዛ (84 በመቶ)፣

ቴዎድሮስ አደባባይ የመኪና ማቆሚያ (G-3) 72 በመቶ፣

ባሻ ወልዴ አካባቢ የመኪና ማቆሚያ (85 በመቶ)፣

ሜክሲኮ የመኪና ማቆሚያ እና ፕላዛ ግንባታ (86 በመቶ)፣

ጎተራ የመኪና ማቆሚያ እና ፕላዛ ግንባታ (52 በመቶ)፣

ኦሎምፒያ የመኪና ማቆሚያ፣ ፕላዛ ግንባታ (98 በመቶ)፣

ቦሌ ወረዳ-5 ሆሊ ሲቲ ህንፃ አካባቢ የመኪና ማቆሚያ (92 በመቶ)፣

ለሚኩራ ወረዳ-8 ፍሬንድሺፕ ህንፃ አካባቢ የመኪና ማቆሚያ (89 በመቶ)፣

የካ ወረዳ-13 ጥቁር አባይ አካባቢ የመኪና ማቆሚያ (92 በመቶ)

እነዚህ በግንባታ ሂደትና በመጨረሻ ምዕራፍ ላይ የሚገኙ የመኪና ማቆሚያዎችና ተርሚናሎች  ሙሉ በሙሉ ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡ አሁን በከተማዋ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ በከፍተኛ ደረጃ የሚያቃልሉና  የትራንስፖርት ፍሰቱን የሚያሳልጡ ሲሆኑ፤ ለመዲናዋም ዘመናዊ ገጽታንና ውበትን እንደሚያላብሷት አያጠራጥርም፡፡

በዘርፉ የተካሄዱ አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፤ በከተሞች ውስጥ 30 በመቶ የሚሆነው የትራፊክ መጨናነቅ የሚፈጠረው በመኪና ማቆሚያ ሥፍራ (ፓርኪንግ) ፍለጋ ነው። ከዚህ አንጻር እኒህ  ግንባታቸው በፍጥነት እየተከናወነ የሚገኙ የመኪና ማቆሚያዎችና ተርሚናሎች በመዲናዋ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ በማስቀረት ምቹና የተሳለጠ የትራንስፖርት ፍሰት ከመፍጠርም ባሻገር  የከተማዋን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነትም እንደሚያሳድጉ  ይታመናል፡፡

በነገራችን ላይ እነዚህ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያዎችና ተርሚናሎች ለዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድል እየፈጠሩ መሆኑም  ሊዘነጋ አይገባም፡፡ በግንባታ ሂደትም ሆነ ተጠናቀው ወደ አገልግሎት ሲገቡ ለዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድሎችን እየከፈቱ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለከተማ አስተዳደሩ ተጨማሪ የገቢ ምንጭም እየሆኑ ነው፡፡  

በመጨረሻም ሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ከተሞችም የመዲናዋን ፈለግ በመከተል በጀመሯቸው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያ ሥፍራዎችና ተርሚናሎች በማካተት የተሳለጠ የትራንስፖርት ሥርዓት ለመፍጠር እንደሚተጉ እምነታችን ነው፡፡


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.