እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረ...

image description
- ውስጥ Current Affairs    0

እንኳን ለኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል አደረሳችሁ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

ትንሣኤ የመሥዋዕትነት፣ የጽናት እና የተስፋ በዓል ነው።

የበደለው ዓለም ነው። የተሠዋው ግን ክርስቶስ ነው። ያጠፋው የሰው ልጅ ነው፣ የካሠው ግን ክርስቶስ ነው። ባለ ዕዳው ሰው ነው። ከፋዩ ግን ክርስቶስ ነው።

የክርስቶስ ሞት አንድም ለማዳን ነው፤ አንድም ለትምህርት ነው። ስለ ብዙዎች ሲባል መሥዋዕትነት ካልተከፈለ ብዙዎችን ማዳን አይቻልም። ሀገርን፣ ሕዝብን፣ ወገንን ማዳን ከተፈለገ መሥዋዕትነት መክፈል ይገባል። ቃል ክርስቶስ በቃሉ ብቻ አልተናገረም። በመስቀል ላይ ውሎ ፍቅሩን በተግባር ገለጠው እንጂ። ራሱ አስታራቂ፣ ራሱ ታራቂ፣ ራሱም መሥዋዕት ሆነ። 

ዛሬ ኢትዮጵያን የሚወድ ሁሉ መሥዋዕት ለመሆን የተዘጋጀ መሆን አለበት። በሌሎች መሥዋዕትነት መጓዝ የኦሪት ሰዎችም አድርገውታል። ሺ በጎችንና ሺ ፍየሎችን ሠውተው ነበረ። አልሆነም እንጂ። ሀገርን ማዳን የሚቻለው ሌሎችን በመሠዋት አይደለም። ራስን በመሠዋት እንጂ። የራስን ጉልበት፣ ጊዜ እና ዕውቀት በመሠዋት እንጂ። የራስን ክብርና ኢጎ በመሠዋት እንጂ።

ሀገርን ለማዳን ወደ ትኅትና፣ ወደ ዕርቅ እና ወደ ምክክር መስቀል አውርዶ ራስን መሠዋት ያስፈልጋል። መስቀል መከራ ነው፤ ስድብ ነው፤ ግርፋት ነው፤ ውርደት ነው። ራሳችንን ለሰላምና ለዕርቅ መንገድ ስናዘጋጅ ከብዙዎች ዘንድ ስድብ፣ ርግማን፣ መከራ፣ ይጠብቀናል። የሚያዋጣን ግን ከሊቶስጥራ እስከ ቀራንዮ የኢትዮጵያን መስቀል መሸከም ነው። ለኢትዮጵያ ትንሣኤ ስንል መስቀሏን መሸከም። 

ትንሣኤ ከጽናት በኋላ የሚገኝ ድል ነው። ከፊቱ የጅምላ ፍርድ አለው፤ ከፊቱ ውግዘት አለው፤ ከፊቱ ግርፋት አለው፤ ከፊቱ መራቆት አለው፤ ከፊቱ መከዳት አለው፤ ከፊቱ የፀሐይ መጨለም፣ የጨረቃ ደም መልበስ፣ የከዋክብትም መርገፍ አለው። በዚህ ሁሉ ግን በሸላቾቹ ፊት ዝም እንደሚል በግ ክርስቶስ በጽናት ቆመ። ስለ ዓላማ ሲባል መከራን ታገሠ። ስለ ሰው ልጅ ሲባል ሁሉን እየቻለ በጽናት ተጓዘ።

ሀገር ጽናት ትፈልጋለች። በመከራዎች እና በውግዘቶች ፊት በጽናት መቆም። በስድብና በንቀት ፊት በጽናት መቆም። እንደ ፀሐይ የሚታዩት ልሂቃን ሲጠፉ፣ እንደ ከዋክብት የሚታዩት ክቡራን ሲረግፉ በጽናት መቆም። አብረው የነበሩ ፈርተውና ተሽጠው ሲከዱ በጽናት መቆም - ሀገር ትፈልጋለች። በሚጸኑት ዘንድ የኢትዮጵያ ትንሣኤ እጅግ ቅርብ ብቻ አይደለም። የሚታይም ነው።

ትንሣኤ ተስፋ ነው። ፈተናው እንደሚያልፍ ተስፋ ይሰጣል። ዓርብን ላየ እሑድ የሚመጣ አይመስልም ነበር። የመቃብሩን ድንጋይ ላየ የሚነሣ አይመስልም ነበር። ማኅተሙን ላየ የሚፈታ አይመስልም ነበር። ጨለማውን ላየ ብርሃን ሩቅ ይመስል ነበር። ሁሉም ግን ተገለበጠ። ታሪክን የታሪኩ ጌታ ለወጠው። 

ተስፋችን በደጅ ነው። ዓርብ ላይ እሑድን እናየዋለን። ከሞት ባሻገር ሕይወትን፣ ከመቃብር አልፈንም ትንሣኤን የምንመለከት ነን። የሚጨበጥ ሕልም የጠራ ምናብ አለን። ስለዚህም ወጀብና አውሎ ነፋስ አያስደንቀንም። ዛሬ ለነገ፣ ሞት ለትንሣኤ ቦታ እንደሚለቁ የምናውቅም፣ የምናምንም ነን።
 
ለኢትዮጵያ ትንሣኤ የሚተጉ ብዙዎች ናቸው። የሕማማቱ ጊዜ እያለፈ ነው። አሁን ዓርብ ወደ ማታ ላይ ነን። ከጸጥታው ቀን በኋላ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ይመጣል። ከሄዱት ብዙዎች ይመለሳሉ። ከተሳሳቱት ብዙዎች ያስተውላሉ። ዓርብ ዕለት በከንቱ የጮኹት ብዙዎች ያፍራሉ። ፈራጆች ይፀፀታሉ። ተገዳዳሪዎች ይበታተናሉ። የመቃብር ጠባቂዎች ይደነግጣሉ። ኢትዮጵያ ግን አይቀሬ በሆነው ትንሣኤ ትነሣለች። 

 ትንሣኤው ከእሥራኤል ለዓለም እንደተገለጠው ሁሉ፣ ኢትዮጵያም ለዓለም ትገለጣለች። 

 የትንሣኤ በዓል የሚያስተምረንም ይሄንኑ ነው።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሚያዝያ 11 ቀን 2017 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)


Comments

ምንም አልተገኘም.

አስተያየቶችዎን ይተዉት.